ኮሌጁ የካንሰር በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከአጋር አካላት ጋር የቅንጅት ሥራዎችን ለመሥራት ቁርጠኛ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ የካንሰር በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከአጋር አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከአፍሪካ የምርምርና ሥልጠና ማዕከል፤ በአፍሪካ በካንሰር በሽታ ዙሪያ ጥናትና ምርምር ከሚያደርጉ ተቋማት ጋር ምክክር አካሂዷል፡፡

የምክክሩ ዓላማ በአፍሪካ ደረጃ ያለውን የካንሰር ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችና ስጋቶች ምንድናቸው?  እንዴት በጋራ በመሥራት ካንሰር ላይ ለውጥ ማምጣት ይቻላል? የሚል ነው፡፡  

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የካንሰርና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ክፍል አስተባባሪ ዶክተር አዳሙ አዲሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ካንሰር በአፍሪካ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

የዛሬው ውይይትም የበሽታውን አሳሳቢነት ለመቀነስ  ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ እንዴት ማተኮር አለብን? በዘርፉ ያሉ ተዋንያን ምን መሥራት አለባቸው? የሚለው ላይ ተወያይቶ መፍትሔ ለማበጀት የተደረገ  መሆኑን ገልፀዋል።

በአፍሪካ የካንሰር በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ መሪዎች ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል ሲሉም ዶክተር አዳሙ አዲሴ ተናግረዋል።

በተለይም ሴቶች ስለጡትና ስለ ማህጸን በር ካንሰር ግንዛቤ እንዲኖራቸው በየጊዜው ምርመራ እንዲያደርጉ እንዲበረታቱ ማድረግ ይገባል ብለዋል። 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በአፍሪካ የካንሰር በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከአጋር አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

በጤና ተቋማት ላይ አገልግሎቱ በብቃት እንዲሰጥ የጤና ባለሙያዎች ከታችኛው የአገልግሎት መስጫ ጀምሮ ምልክቶችን በማወቅ ቶሎ አስፈላጊውን ሕክምና ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በተለይ ለጤና ባለሙያዎች አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት፤ በሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ ተካቶ እንዲሰጥ እየተደረገ ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም