ተመራቂዎች በሰለጠኑበት መስክ ሕዝብና አገርን በታማኝነት በማገልገል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂዎች በሰለጠኑበት መስክ ሕዝብና አገርን በታማኝነት በማገልገል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፡- ተመራቂ ተማሪዎች በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ለትውልድ የሚተርፍ ስራ በማከናወን ሕዝብና አገርን በታማኝነት በማገልገል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 8ሺህ 524 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።
በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ አባል ወይዘሮ አስቴር ዘውዴ እንዳሉት፤ መማር፣ መመራመርና ዕውቀትን መገበየት የአገርን ዕድገት ያፋጥናል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ፍላጎቶቿን ለማሟላትና የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ሳይንሳዊ በሆነ አግባብ ለመፍታት ጥረት የሚያደርግ ሀገር ወዳድ ትውልድ ያስፈልጋታል ብለዋል።
ለዚህም የዛሬ ምሩቃን ወደ ስራው ዓለም ሲገቡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት፤ ለትውልድ የሚተርፍ ስራ በማከናወን ሕዝብና አገርን በታማኝነት በማገልገል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው 8 ሺህ 524 ተማሪዎች በመደበኛው፣ በክረምት፣ በተከታታይና በርቀት ትምህርት መርሃ ግብሮች ያስተማራቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
ተመራቂዎቹ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመጀመሪያ፣ ሁለተኛ፣ ሶስተኛ ዲግሪና በሰርተፍኬት የተመረቁ ሲሆን፤ ከመካከላቸውም 3 ሺህ 34 ሴቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የመውጫ ፈተና ካስፈተናቸው ተማሪዎችም ከ93 በመቶ በላይ ማሳለፉን ጠቅሰው፤ ተመራቂ ተማሪዎችም በተመረቁበት የሙያ መስክ ሕዝባቸውንና አገራቸውን በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ከተመራቂዎች መካከል በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርት በሁለተኛ ዲግሪ የተማረችው ሰላማዊት ተመስገን በሰጠችው አስተያየት፤ መማርና ማወቅ ትልቁ ዓላማ ከራስ ባለፈ ሀገርን መጥቀም እንደሆነ ተናግራለች።
እኔም በተማርኩበት የትምህርት ዘርፍ ሀገሬንና ህዝቧን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ስትል ገልፃለች።
የመጀመሪያ ዲግሪውን በመካኒካል ኢንጂነሪንግ ሰልጥኖ እንደተመረቀ የተናገረው ሚኪያስ መንግስት በበኩሉ፤ በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ሀገራችን ትልቅ ደረጃ እንድትደርስ አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብሏል።
በተማረበት የሙያ ዘርፍም የመንግስትን ስራ ሳይጠብቅ በራሱ ስራ ለመፍጠር ከወዲሁ ማቀዱንም አስታውቋል።
ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከ28 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች እያስተማረ እንደሚገኝም ተመልክቷል።