በድሬዳዋ አስተዳደር ምቹ የሥራና የመኖሪያ አካባቢዎች ለመፍጠር ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ድርሻቸውን መወጣት አለባቸው - ከንቲባ ከድር

ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ አስተዳደር ምቹ የሥራና የመኖሪያ አካባቢዎች ለመፍጠር  ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ ከንቲባ ከድር ጁሃር አሳሰቡ።

ከንቲባ ከድር ጁሃርን ጨምሮ ከፍተኛ የአመራር አባላት የተሳተፉበት የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዛሬ በአስተዳደሩ ስር በሚገኙ ተቋማት ተካሄዷል።

በዚህም ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል፣ አዲሱ ምድር ባቡርና በሌሎች ተቋማት የጥላ፣ የውበት፣ የፍራፍሬና የደን ችግኞች ተተክለዋል።

ከንቲባ ከድር በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ውብና ተስማሚ ከተማ እና የሥራ ተቋማት ለመፍጠር መሠረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ምቹ የስራ አካባቢን በመፍጠር ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት መርሐ ግብሩ አጋዥ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመሆኑም ድሬዳዋን ምቹና ተስማሚ የመኖሪያና የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግና ተቋማት የስራ አካባቢያቸውን ምቹ ለማድረግ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።

በችግኝ ተከላው የተሳተፉ ተቋማት ለተከሏቸው ችግኞች እንክብካቤ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአስተዳደሩ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ በመከላከል ረገድ ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግሥት ተቋማትና የህክምና ማዕከላት ለተገልጋዮች ምቹ ሆነው አገልግሎት ለመስጠት እያገዙ መሆኑንም በመጠቆም መርሐ ግብሩ በልዩ ትኩረት በመተግበር ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

በችግኝ ተከላው የተሳተፉ አካላትም በድሬዳዋ የሚታየውን አበረታች ውጤት ለማጠናከር፣ የልማትና የጋራ ትስስርን ለማፅናት በተከላው ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ለትውልድ የተሻለ አገርና አካባቢ ለማውረስ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር መሳተፍ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በከተማዋ በተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር  ከችግኝ መትከል ባሻገር፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የሆኑ የደም ልገሳና ነፃ የጤና ምርመራ በተጓዳኝ ተካሄዷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም