በዞኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ164 በላይ አዳዲስ የአቅመ ደካሞች ቤቶች ተገንብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ164 በላይ አዳዲስ የአቅመ ደካሞች ቤቶች ተገንብተዋል
ነገሌ ቦረና፤ ሀምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ቦረና ዞን በዞኑ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ164 በላይ አዳዲስ የአቅመ ደካሞች ቤቶች መገንባታቸውን የዞኑ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ነመራ ቶሎሳ፣ በዞኑ በዚህ ክረምት ከ15 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች መሰማራታቸውን ገልጸዋል።
ከሀምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ መጀመሩንም ጠቅሰው ዘንድሮ በዞኑ ከአንድ ሺህ 790 በላይ የአቅመ ደካሞች ቤቶችን ለመገንባትና ለማደስ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
እስካሁን በበጎ ፈቃደኞቹ ድጋፍና ትብብር ከ164 በላይ አዳዲስ የአቅመ ደካማ ሰዎች ቤቶች ግንባታ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ከዚህም በላፈ በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚተዳደሩ አባወራዎችና እማወራዎች 23 የወተት ላሞችና 200 እንቁላል ጣይ ዶሮዎች ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ወላጆቻቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚተዳደሩ 222 ህጻናት 111 ደርዘን ደብተርና 61 እሽግ እስኪርብቶ መከፋፈሉንም ጠቁመዋል።
በዞኑ እስካሁን የተከናኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች በጋራ ድጋፍና ትብብር ብዙ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑንም ገልጸዋል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው አገልግሎቱ ችግራቸውን እያቃለላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የነገሌ ቦረና ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ፈታ ነጋሽ፣ በጉልበት ስራ እሳቸውን ጨምሮ 7 ቤተሰቦቻቸውን በማስተዳደር ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።
የሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ያረጀ መኖሪያ ቤታቸውን ለማሳደስ ባለመቻለቸው ችግር ውስጥ መቆየታቸውን አንስተዋል።
ዘንድሮ በመንግስትና በህዝብ ትብብር 21 የቆርቆሮ ክዳን ቤት ተሰራልን፣ እኔና ቤተሰቦቼም በደስታና በተስፋ መኖር ጀምረናል ብለዋል፡፡
የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ባቦ ቁልቁሉ፣ የሚኖሩበትን ቤት ለማደስ አቅም ስለሌላቸው በክረምት ለዝናብ በበጋ ለጸሀይና ለነፋስ ሲጋለጡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ችግሬን የተረዱት በጎ ፈቃደኞች 32 ክዳን ቆርቆሮ ቤት ሰሩልኝ፣ የመረዳዳት ባህላችን የሚያኮራ በመሆኑ በተደረገልኝ ድጋፍ ሁሉ ተደስቻለሁ ብለዋል፡፡