ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ተቋማት ንብረት የማስወገድ ስራቸውን በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት ብቻ ያካሒዳሉ - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ተቋማት ንብረት የማስወገድ ስራቸውን በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት ብቻ ያካሒዳሉ - ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ተቋማት ንብረት የማስወገድ ስራቸውን በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት ብቻ እንደሚያካሒዱ የመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።
የመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወልደአብ ደምሴ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት የመንግሥት ግዥና አስተዳደር ሥርዓትን ዘመናዊ ከማድረግ አንፃር አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በአሁኑ ወቅትም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በ169 ተቋማት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የንብረት ማስወገድ ተግባሩ አሁንም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ባለመሆኑ ውጤታማነቱ በቂ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።
ለተቋማት የግዥ ስርዓት እንዲያገለግል የለማው (e-GP) የተሰኘው ቴክኖሎጂ ከግዥ ስራው ጎን ለጎን የንብረት ማስወገድ ተግባሩንም ያካተተ በመሆኑ ዘርፉን በማዘመን ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
በመሆኑም ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ተቋማት ንብረት የሚያስወግዱበት መንገድ በዚሁ ቴክኖሎጂ በተደገፈ አሰራር ብቻ እንደሚሆን አስታውቀዋል።
ሌላው ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም የጸደቀው የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ የተቋሙን የአሰራር ስርዓት የሚያዘምንና የሚያቀላጥፍ በመሆኑ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ ይገባል ብለዋል።
አዋጁ በዋናነት ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የግዥና ንብረት ማስወገድ አሰራር መተግበር፣ ለሀገር ውስጥ አምራቾችና ምርት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ መልሶ በመጠቀም ሒደት ከብክለት የጸዳ አረንጓዴ የማስወገድ ስርዓትን እውን የሚያደርግ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በዚህ ሒደት በተለይም የሀገር ውስጥ አምራቾችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን የሚያበረታታ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ረገድ አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል።
የጸደቀው አዋጅ የተቋሙን የአሰራር ስርዓት በማሻሻል በዘርፉ የሚፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደሚያቃልልም ገልጸዋል።
አዋጁን ተከትሎ የሚወጡ የአሰራር መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው ከ2017 በጀት ዓመት ጀምሮ የተቋሙ አሰራር ሙሉ በሙሉ በአዲሱ አዋጅ ላይ ተመስርቶ የሚከናወን መሆኑን አስታውቀዋል።