ምክር ቤቱ በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት የተጎዱ  ወገኖች በዘላቂነት ለማቋቋም ድጋፉን እንደሚያጠናክር  አስታወቀ

ሳውላ፤ ሐምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በዘላቂነት ለማቋቋም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ። 

ምክር ቤቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በቦታው ተገኝቶ በማጽናናት የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

ድጋፉን ያስረከቡት የምክር ቤቱ አባልና የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ ኮሬ፤  በገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰተው አደጋ በደረሰው ጉዳት ምክር ቤቱ ማዘኑን ገልጸዋል።

የደረሰው አደጋ እጅግ ከባድና ልብ የሚሰብር ነው ያሉት ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ ፤ ምክር ቤቱ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ መስጠቱን አስታውቀዋል።

በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ምክር ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። 


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ  ማሃዲ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ የተሰማውን ሀዘን ሲገልጽ መቆየቱንና ተጎጂዎችን ለማጽናናት በስፍራው መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ከፌዴራል መንግስት ጀምሮ መላው ኢትዮጵያውያን ባለን የመረዳዳት ባህልና እሴት መሰረት ለወገን ደራሽ መሆናቸውን በስፍራው እየተደረገ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ ማየት ችለናል ብለዋል።

በአደጋው ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ  ሴቶች፣ ህጻናት አካል ጉዳተኞችና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካላት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።


 

የምክር ቤት አባላት በእረፍት ላይ በመሆናቸው እንጂ በአካል እዚህ ተገኝተው ሀዘናቸውን መግለጽ እንደሚፈልጉ የተናገሩት ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአባላት ተሳትፎ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ባንጉ ናቸው።

 አባላቱ ለወገናቸው ደራሽ መሆናቸውን ለመግለጽ ካሉበት ሆነው 340 ሺህ ብር በማዋጣት ለተጎዱ ወገኖች እንዲደርስ መላካቸውን ገልጸዋል።


 

የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ከረዩ ባናታ በበኩላቸው፤ የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት እስከታችኛው ባለሙያ ድረስ አደጋውን ከሰሙበት ጊዜ አንስቶ ተጎጂዎችን ለመደገፍ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ክልሉና ዞኑ የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያከናውኑትን ስራ በመደገፍ እንደሚሰራም ተናግረዋል።


 

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጅነር ዳግማዊ አየለ ድጋፉን ከተረከቡ በኋላ እንዳሉት፤ አደጋው ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ መላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በስፍራው በመገኘት ላደረገው ድጋፍ በተጎጂዎቹ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም