የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ትውልድ የመገንባት ሚናን እየተወጣ ያለ ተቋም ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአገሪቱ ሁለንተናዊ ታሪክ፣ እድገትና ትውልድ የመቅረጽ ጉልህ ሚና የነበረውና ይህን አጠናክሮ እየቀጠለ ያለ ተቋም እንደሆነ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።

የልጆችን የንባብ ባህል ለማዳበር ከዲጂታል ዓለም በተጨማሪ በወረቀት፣ ብራናና በሌሎች የተጻፉ ጽሑፎችን እንዲያነቡ ማድረግ ይገባል ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ናቸው። 


 

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተዘጋጀ "ብላቴናት" የተሰኘ ባለቀለም የልጆች መጽሔት  ዛሬ ተመርቋል። 

በመጽሔት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ ሚኒስትሮች፣ የመገናኛ ብዙኃን አመራሮች፣ ደራሲያን፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የእድሜውን ያህል አንጋፋና ጥበብ የተሸከመ የታሪክ ማኅደር የሆነ ተቋም ነው። 


 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት እንዲሁም ብዝኃነታችን ለአንድነታችን መሠረት መሆኑን ያበሰረ ተቋም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አገር ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም አንስተዋል።

ተቋሙ የጀመረው ሥራ ለአገር የሚመጥን ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ሌሎችም የተቋሙን አርዓያነት በመከተል ቀላል በሆነ መንገድ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተለያዩ ሕትመቶች ለልጆች ተደራሽ ማድረግ አለባቸው ብለዋል። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት  ላለፉት ሺህ ዘመናት የመላው ዓለም እውቀት የተከማቸው በጽሑፍ በመሆኑ የዲጂታል ዓለሙን ከንባብ ባህል ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል ብለዋል።

ልጆች የንባብ ባህልን ካላዳበሩ ዓለም ካከማቻቸው እውቀት የተለዩ ስለሚሆኑ ወላጆች፣ መገናኛ ብዙኃን ልጆችን ከወረቀት ጋር ማቀራረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል። 

የዲጂታል ቴክኖሎጂ አንድን ነገር በፍጥነት ለማግኘት እንዲሁም ከጽህፈት ጋር የተገናኘ ጥበብ የማስታወስ ችሎታን ለማሳደግ የሚጠቅሙ በመሆኑ ልጆች ሁለቱን አቀናጅተው እንዲሄዱ ማድረግ ይገባል ሲሉም አክለዋል።

የንባብ ባህልን ለማሳደግ ልጆች በሚውሉበት ሥፍራ ጽሑፎችን ማስቀመጥ አስፈላጊ እንደሆነ አንስተው፤ ለዚህም ከወላጆች ጀምሮ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው፤  የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ላለፉት ስምንት አሥርት ዓመታት አገርን ሲገነባና ትውልድ ሲያንጽ መቆየቱን አንስተዋል። 


 

በ83 ዓመት ጉዞው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በየሳምንቱ በልጆች አምድ አስተማሪ ይዘቶች ሲያቀርብ እንደቆየ ተናግረው፤ አገር ተረካቢ ህፃናት የሕትመት ሚዲያ እንዲኖራቸው "ብላቴናን" ለማሳተም መብቃቱን ተናግረዋል። 

መጽሔቱ በትምህርት ቤቶችና በሕዝብ ቤተ-መጽሐፍት አማካኝነት የሚሰራጭ ሲሆን፤ በአዟሪዎች ማግኘት የሚቻል መሆኑንም ገልፀዋል። 

ልጆች እየተዝናኑ እውቀት የሚገበዩበት፣ ስለአገራቸው ወጥ አረዳድ እንዲኖራቸው፣ በስነ-ምግባር እንዲታነፁና አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር አቅም የሚፈጥሩበት መጽሔት መሆኑን ተናግረዋል። 

የይዘት ዝግጅቱ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች፣ በስነ-ጽሑፍ ባለሙያዎችና ሰዓሊያን የሚሳተፉበትና በቀጣይ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎች ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

የቅድመ መደበኛ መምህርት የሆነችው መምህርት ዙፋን ታምር እና የልጆች ፕሮግራም አዘጋጅና የልጆች መጽሐፍ ደራሲ አስረስ በቀለ በበኩላቸው፤ መጽሔቱ የልጆችን የንባብ ባህል ለማሳደግ የሚረዳ ነው።


 

የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ መልዕክተ ኃይሉ እና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሜሮን ሀብታሙ መጽሔቱ በቀለማት የተዋበ ሆኖ መምጣቱ ንባብን የሚያበረታታ መሆኑን አንስተው፤ ሌሎችም በመሰል ተግባር በመሰማራት ትውልዱ በትክክለኛው መንገድ እንዲጓዝ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።


 

"ብላቴናት" በመላ ሀገሪቱ የሚሰራጭ፣ በቀጣይ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖሩባቸው አገራት ተደራሽ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን፤ አምዶችን በመከፋፈል  ከ3 እስከ 9 ዓመት በላይ የሚሆኑ  ልጆችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑም  ተገልጿል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም