ብሄረሰብ አስተዳደሩ ከ48 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወባ በሽታ ለመጠበቅ  የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል

ሰቆጣ፤ ሐምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፡- በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ48 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወባ በሽታ ለመጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን የብሄረሰብ  የአስተዳደሩ ጤና መምሪያ አስታወቀ። 

የመምሪያው የወባ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ አበበ በለጠ ለኢዜአ እንደገለጹት፤  በብሄረሰብ አስተዳደሩ የወባ በሽታን  የወባ መከላከልና ቁጥጥር ስራ ሲከናወን ቆይቷል። 


 

በዚህም ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ  ሰሃላ፣ ዝቋላና አበርገሌ ወረዳዎች በሚገኙ 25 ቀበሌዎች ከሰኔ 23   እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የፀረ ወባ ትንኝ መከላከያ ኬሚካል ርጭት መደረጉን ተናግረዋል። 

በዚህም  14 ሺህ 420 ቤቶች ላይ የፀረ ወባ ኬሚካል መርጨቱን አመልክተው፤ በተጨማሪም በጤና ሚኒስቴር በኩል 36 ሺህ 111 የወባ ትንኝ መከላከያ  አጎበር ቀርቦ መሰራጨቱን አስታውቀዋል።

በተከናወኑት የመከለካል ስራዎች ከ48 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወባ በሽታ እንዲጠበቁ መደረጉን  አስረድተዋል። 

ህብረተሰቡም የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር በአግባቡ ሊጠቀም እንደሚገባና የወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ ስፍራዎችን  የማዳፈን ስራ ማከናወን እንዳለበት  አሳስበዋል። 

የዝቋላ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ እስጢፋኖስ ወንዳየ እንዳሉት፤ የወባ ስግጭቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወረዳው ሦስት ቀበሌዎች ላይ የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት ከመደረጉም ባለፈ 22 ሺህ አጎበር ቀርቧል። 


 

በዚህም 2 ሺህ 556 ቤቶች ላይ ርጭት መደረጉን ገልፀው፤ የወባ መራቢያ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ቦታዎችን የማዳፈን ስራ የክረምት በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ እየተሰራ ነው ብለዋል። 

በወረዳው 01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ መኳንንቴ ገብሩ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት የበጋ ወራት በአካባቢያቸው የወባ በሽታ ስርጭት ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል። 

በአካባቢያቸው የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት መደረጉ ደግሞ የክረምት ወራትን ከወባ በሽታ ያለ ስጋት እንዲያሳልፉ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። 

''በአካባቢያቸው ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ቦታዎችን የማዳፈን ስራ እየሰራን ነው'' ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም