በምክክር ሀገራዊ አንድነትን እውን ለማድረግ የተጀመረው ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን ዜጎች ንቁ ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል- ዶክተር ተገኘወርቅ ጌቱ

ድሬዳዋ ሐምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፡- በአካታችና ነጻ ህዝባዊ ምክክር ሀገራዊ አንድነትን እውን ለማድረግ የተጀመረው ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን ዜጎች ንቁ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽነር ዶክተር ተገኘወርቅ ጌቱ ተናገሩ።

ኮሚሽኑ በድሬዳዋ አስተዳደር እና በሐረሪ ክልል ከነሐሴ ስድስት ጀምሮ አጀንዳ ለማሰባሰብ ምክክር ያካሂዳል።

በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በድሬዳዋ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ውይይት ላይ ለሚሳተፉትና ድሬዳዋ ከሚገኙት የሲቪል ማህበራት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ተገኘወርቅ ጌቱ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ፤ኮሚሽኑ በየክልሉና በከተማ አስተዳደሮች በህዝብ ከተመረጡ ወኪሎች ጋር ለአገራዊው ምክክር የሚጠቅሙ አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ እያካሄደ ነው።

ባለፈው ሳምንት ከቤኒሻንጉል እና ከጋምቤላ ክልሎች ከተመረጡ የህዝብ ወኪሎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበራት እና ከሚመለከታቸው ወኪሎች ጋር በመምከር አጀንዳ አሰባስቦ አጠናቋል ብለዋል።

ከነሐሴ ስድስት ጀምሮ በድሬዳዋ አስተዳደር እና በሐረሪ ክልል አጀንዳ ለማሰባሰብ የውይይት መድረኮች እንደሚያካሂድም አስረድተዋል።

ነጻ፣ አካታች እና ገለልተኛ በሆነው መንገድ ከሚካሄደው ውይይት አገራዊ መግባባት የሚፈጥሩ አጀንዳዎች እንደሚሰበሰቡም ነው ዶክተር ተገኘወርቅ የገለፁት።

ተቻችለን፣ ተረጋግተንና ተደማምጠን በመወያየት ብሎም ሰጥተን በመቀበል ነው ወደፊት መዝለቅ የምንችለው ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በሰላም፣ በመመካከርና በመተባበር ከተሰራ አገርን የሚያፀኑ ውጤቶችን ማግኘት እንችላለን ብለዋል።

እንደ ኮሚሽነር ተገኘወርቅ ጌቱ (ዶ/ር) ገለፃ ድህነትና በሰላም እጦት መድቀቅ እንዲያከትም ሁሉም  በሀገራዊ ምክክሩ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት።

የሲቪል ማህበራት ባላቸው ህዝባዊ ኃላፊነት እና ልምድ በአጀንዳ ማሰባሰቡ ላይ የነቃ ተሳትፏቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የኮሚሽኑ የአጀንዳ እና የምክክር አስተባባሪ አቶ ተመስገን አብዲሳ ከነሐሴ ስድስት ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት አስቀድመው ከድሬዳዋ አስተዳደር ከከተማ እና ገጠር ወረዳዎች በህዝብ ከተመረጡ ወኪሎች ጋር አጀንዳ የማሰባሰብ ውይይት ይካሄዳል ብለዋል።

በውይይቱም የሁሉም ህብረተሰብ ወኪሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበራት፣ የመንግስት አካላት እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደሚሳተፉ አስረድተዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ የውይይት መድረክ ላይ የሚሳተፉት አካላት በነፃነት፣ በገለልተኝነት እና በእኩልነት ለሀገራዊ ምክክሩ የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን ያቀርባሉ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም