በአማራ ልማት ማህበር (አልማ) የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ

ደሴ ፤ ሐምሌ 27/ 2016 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ወሎ ዞንና አካባቢው በአማራ ልማት ማህበር (አልማ) የተገነቡ 21 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን በማህበሩ የደቡብ ወሎ ዞንና አካባቢው ማስተባበሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አልማ የመንግስትን የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍ እያገዘ  ሲሆን፤ በዚህም ህዝብን ተጠቃሚ በሚያደርጉና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል።

ማህበሩ ነባርና አዳዲስ አባላትን እንዲሁም የልማት አጋሮችን ጭምር በማስተባበር መንግስት ከሚሰራቸው የልማት ሥራዎች ጎን ለጎን የልማት ክፍተቶችን ለይቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትንና የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። ፡

በዚህም 63 የትምህርትና የጤና የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ69 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ 21 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት ክፍት መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ለአገልግሎት ከበቁት መካከል 14ቱ የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻያና ማስፋፊያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ቀሪዎቹም የአንድ አዲስ ጤና ጣቢያ ግንባታ፣ የስድስት ጤና ጣቢያዎች ደረጃ ማሻሻያና ማስፋፊያዎች ናቸው ብለዋል፡፡

የተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች ከ158 ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ያሉት ኃላፊው፤ ቀሪ ፕሮጀክቶችንም በ2017 በጀት ዓመት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በደሴ ዙሪያ ወረዳ የቀበሌ 01 ነዋሪ አቶ ሀሰን አልይ በሰጡት አስተያየት፤  በአካባቢያቸው ያለው አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከደረጃ በታች በመሆኑ በልጆቻቸው ትምህርት ላይ ጫና አሳድሮ መቆየቱን ገልጸዋል።

ዘንድሮ በአልማ በተገነባ ባለ አንድ ወለል ህንጻ  ግንባታ የትምህርት ቤቱ ደረጃ በመሻሻሉ ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

ሌላው የቃሉ ወረዳ 023 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሁሴን እሸቱ እንዳሉት፤ አልማ በየአካባቢያቸው የሚገኘውን ትምህርት ቤት ደረጃ በማሻሻል ልጆቻቸው በተሻለ ትምህርት ቤት እንዲማሩ አመቻችቷል።

''እኛም በጉልበታችንና በገንዘባችን የድርሻችንን ተሳትፎ አድርገናል'' ብለዋል።

በማህበሩ የደቡብ ወሎና አካባቢው ማስተባበሪያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ370 ሺህ ከሚበልጡ አባላት ከ111 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ከማስተባባሪያው ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም