ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ በበጎ ፍቃድ ተግባራት በመሰማራት ህዝባዊነቱን እያስመሰከረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ በበጎ ፍቃድ ተግባራት በመሰማራት ህዝባዊነቱን እያስመሰከረ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ በበጎ ፍቃድ ተግባራት በመሳተፍ ህዝባዊነቱን እያስመሰከረ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሮችና አባላት በዛሬው ዕለት በኮልፌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ማዕከል በመገኘት አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሁሉም የፖሊስ ሰራዊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር ) አነሳሽነት የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ገቢራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ፖሊስ መንግስት የጀመረውን ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ መርሀ ግብር በመደገፍ ችግኝ ይተክላል፤ ጽድቀታቸውንም ይከታተላል ብለዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዓለም ላይ ያስከተለውን ጎርፍ ድርቅና መሰል የተፈጥሮ አደጋ ለመከላከል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ድርሻው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መርሀ ግብሩ ምግብ ነክ የሆኑ ችግኞችን በመትከል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ፕሮጀክት በመሆኑ ፖሊስ በትኩረት የሚሰራበት ማህበራዊ ሃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የኢትዮጵያ የደን ሽፋን እየተሻሻለ መምጣቱን የገለጹት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ፤ ከልማት ተግባራት ባሻገር ፖሊስ በመደበኛ ሥራው የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ አለኝታነቱን አረጋግጧል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሰራዊት ሰፊ ቁጥር ያለውና በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ከመደበኛ ሥራው ባሻገር በማህበራዊ አገልግሎቱ ህዝባዊነቱን ማረጋገጥ አስችሎታል ብለዋል፡፡
በመሆኑም በመንግስት ከተሰጠው የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ተልዕኮ ባሻገር በሌሎች ሀገራዊ በጎ አድራጎት ሥራዎች የሚኖረው ተሳትፎ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የአድማ ብተና ፖሊስ መምሪያ ሬጅመንት 1 ምክትል አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር አባተ ፈለቀ ፖሊስ እንደ ዜጋ በችግኝ ተከላ አሻራውን በማሳረፍ የቀጣዩ ትውልድ አርአያ መሆኑን በተግባር ያሳያል ብለዋል፡፡
ረዳት ሳጅን አረብ ሁሴን በበኩላቸው በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ እንደ ፖሊስ ማንኛውንም መስዋዕትነት በመክፈል ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች አገር ለማስከበር እንሰራለን ብለዋል፡፡
አረንጓዴ አሻራ ህይወትን ማስቀጠል ነው የሚሉት የፖሊስ አባላቱ፤ የዜጎችን ደህንነተ ከመጠበቅ ባለፈ ሰው ተኮር በሆኑ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል፡፡
የፖሊስ ሰራዊቱ ችግኝ ከመትከል ባለፈ የተተከሉትን በመንከባከብ ለውጤት ማብቃት የሚያስችል መርሀ ግብር ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡