የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በምግብ እራስን የመቻል ዓላማን የሚያሳካ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በምግብ እራስን የመቻል ዓላማን የሚያሳካ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በምግብ እራስን የመቻል ዓላማን የሚያሳካ መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በማእከላዊ ኢትዮጵያ ምስራቅ ጉራጌ ዞን የክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባራት ሥራዎችን አስጀምረዋል።
አፈ-ጉባዔው ከተለያዩ የፌዴራልና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በተጠሪ ተቋማት የሚሰሩ የአቅመ ደካሞች ቤት ዕድሳት ስራዎች በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቁ ገልጸዋል።
በተጨማሪም 300 ለሚጠጉ ተማሪዎች ለ2017 ዓ.ም የሚሆኑ የትምህርት ቁሳቁሶች መበርከቱን ገልጸዋል።
በቡታጅራ ከተማ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ሥራዎችን በማከናወናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገለጸዋል።
ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን ገልጸው፤ የተጀመሩ የልማት እንዲሁም ሰላምን የማጽናት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ አካባቢን ከመጠበቅ ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ትግል አካል መሆኑን አስረድተዋል።
አገራት እራሳቸውን በምግብ እስካልቻሉ ድረስ ከጥገኝነት ሊወጡ አይችሉም ያሉት አፈ ጉባኤው ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በምግብ እራስን የመቻል አላማን የሚያሳካ መሆኑን ተናግረዋል።
የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ የሞት ሽረት መሆኑን ገልጸው ለዚህም የአረንጓዴ አሻራ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
መንግሥት የገባውን ቃል በሙሉ ይተገብራል ያሉት አፈ-ጉባዔው፤ ለዚህም በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሉ ለሚያከናውናቸው የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ምስጋና አቅርበዋል።
የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ምርታማነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ሰላምን የማጽናት እና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማጎልበት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ነሐሴ 13 ቀን 2016 ክልሉ የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአንድ ጀምበር 2 ነጥብ 5 ሚልዮን ሰው የሚሳተፍበት የችግኝ ተከላ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
ለዚህም የመትከያ ቦታዎችን የመለየትና ጉድጓዶችን የማዘጋጀት ስራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
አፈ-ጉባዔ አገኘው ተሻገር ከተለያዩ የፌዴራልና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን የቡታጅራ ከተማ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።