በምክክር መድረኩ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመን በመግባባት ለዘላቂ ሠላም የድርሻችንን እንወጣለን 

ጋምቤላ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፡- በምክክር መድረኩ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በመግባባት ለአገራዊ ዘላቂ ሠላም የድርሻቸውን እንደሚወጡ በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል እያካሄደ ያለው አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እንደቀጠለ ነው።

በምክክሩ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ከምንም በላይ የህዝብና የአገርን ዘላቂ ሠላምና ጥቅም በሚያረጋገጡ ጉዳዮች ሃሳብ በማዋጣት ድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል የኢዜማ ተወካይ ኮማንደር ጋድቤል ቦል እንዳሉት፤ በምክክሩ ህዝብና አገርን ይጠቅማሉ ያሏቸውን ሀሳብ  አዋጥተዋል። 


 

''ከህዝብና ከአገር የሚበልጥ ነገር የለም'' ያሉት ኮማንደር ጋድቤል፣ ሁላችንም በመግባባት የአገሪቷን ሠላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የህዝብና የአገርን ሠላም ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ብሔራዊ ዴሞክራሲ ንቅናቄ/ ጋብዴን/ ተወካይ አቶ ኡቦንግ ኡሞድ ናቸው። 


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየተካሄደ ያለው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ኢትዮጵያ ከችግር የምትወጣበት መንገድ መሆኑን እንደሚያምኑ ተናግረዋል።  

እንደ ፖለቲካ ፓርቲም የህዝብና የአገር ሠላምና ብሔራዊ ጥቅም በሚነኩ ጉዳዮች አንድ ዓይነት አቋም መያዝ ይጠበቅብናል ብለዋል አቶ ኡቦንግ።

በፖለቲካው ዓለም በምርጫ አሸንፎ መምራት የምትችለው ህዝብና አገር ሠላም  ሲሆን ብቻ ነው ያሉት ተወካዩ፤ ሁላችንም ለአገር ዘላቂ ሠላም ቅድሚያ ሰጥተን መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ጋህነን/ተወካይ አቶ ኡኮች ኡሞድ፤ የአገርን ችግር  ለመፍታት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመግባባት ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ልንሰራ ይገባናል ብለዋል።


 

''የማያግባቡ ሃሳቦችን በኃይል አማራጭ ለመፍታት የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው'' ያሉት ተወካዩ፣ በምክክር መድረኩ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀምና መግባባት ላይ መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም