በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በርካታ ሜዳሊያዎችን ያገኙ የኢትዮጵያ አትሌቶች - ኢዜአ አማርኛ
በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በርካታ ሜዳሊያዎችን ያገኙ የኢትዮጵያ አትሌቶች
ኢትዮጵያ በፓሪስ እየተካሄደ የሚገኘውን ጨምሮ በኦሊምፒክ መድረክ ስትሳተፍ ለ15ኛ ጊዜ ነው።
በአውስትራሊያ ሜልቦርን እ.አ.አ በ1956 የተካሄደው 16ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ያደረገችበት ታሪካዊ ሁነት ነው።
እ.አ.አ. በ1960 በሮም በተደረገው 17ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች አትሌት አበበ ቢቂላ በማራቶን በባዶ እግሩ በፈጸመው አኩሪ ገድል ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅና ታሪካዊ ሜዳሊያ አስገኝቷል። አትሌቱ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ወርቅ ያገኘ የመጀመሪያው አፍሪካዊም ሆኗል።
አትሌት አበበ ከአራት ዓመት በኋላ በቶኪዮ በተካሄደው 18ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በማራቶን ክብሩን በማስጠበቅ የወርቅ ሜዳሊያውን በድጋሚ አግኝቷል።
ኢትዮጵያና ኦሊምፒክ ሲታወሱ አበበ ቢቂላ በሰራው ታሪክ በትውልዶች መካከል እየተዘከረ ይኖራል።
ኢትዮጵያ በፓሪስ እየተደረገ ባለው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ10000 ሜትር ወንዶች ፍጻሜ በአትሌት በሪሁ አረጋዊ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።
የበሪሁንን ጨምሮ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች 23 የወርቅ፣ 13 የብርና 23 የነሐስ በድምሩ 59 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች። ሁሉም ሜዳሊያዎች የተገኙት በአትሌቲክስ ስፖርት ነው።
በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በማራቶን ወንዶች የሚወዳደረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በኦሊምፒክ ተሳትፎው 3 ወርቅ እና 1 የብር በድምሩ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በርካታ ሜዳሊያዎችን ያገኘ ኢትዮጵያዊ አትሌት ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል።
አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ 3 የወርቅና 3 የነሐስ በድምሩ 6 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ሌላኛዋ አትሌት መሰረት ደፋር 2 የወርቅ እና 1 የብር በድምሩ 3 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሶስተኛ ስፍራን ይዛለች።
የወቅቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እና ማርሽ ቀያሪው ምሩጽ ይፍጠር በተመሳሳይ 2 የወርቅና 1 የነሐስ በድምሩ 3 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
አትሌት አበበ ቢቂላና ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በተመሳሳይ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል።
ማሞ ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ እሸቱ ቱራ፣ ፊጣ ባይሳ፣ የወቅቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ ኮማንደር አትሌት ጌጤ ዋሚ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ አልማዝ አያና፣ ሰለሞን ባረጋና ጉዳፍ ፀጋይ ለኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ሜዳሊያ ካስገኙ አትሌቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በሚቆየው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በአትሌቶቿ ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል።