ከ157 ቶን በላይ የኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪክ ቆሻሻ ተወግዷል - ኢዜአ አማርኛ
ከ157 ቶን በላይ የኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪክ ቆሻሻ ተወግዷል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት ከ157 ቶን በላይ የኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪክ ቆሻሻ መወገዱን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
የአገልግሎት ጊዜያቸው የተጠናቀቀ የኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪክ ዕቃዎች በአግባቡ ካልተወገዱ ለአካባቢ ብክለትና ለጤና ጠንቅ እንደሚሆኑ ይነገራል።
በዚህም መሰረት የኤሌክትሮኒክስና የኤሌክትሪክ ቆሻሻን የማስወገድ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።
በባለስልጣኑ የአካባቢ ህግ ተከባሪነት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አዲሱ ጥበቡ፤ የአካባቢ ጥበቃ የሁሉም በመሆኑ የብክለትና የንጽህና መጓደል ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን በጥንቃቄ ማስወገድ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ በተለይም የኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪክ ቆሻሻ አካባቢን ከማቆሸሽ አልፎ ለጤና አደገኛ በመሆኑ የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የማስወገድ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪክ ቆሻሻ ለማስወገድ የሚፈልግ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ከአካባቢ ጥበቃ ፈቃድ መውሰድ ግዴታ መሆኑን ጠቅሰው በዚሁ መሰረት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ157 ቶን በላይ የኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪክ ቆሻሻ መወገዱን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪክ ቆሻሻ ክምችት እየተበራከተ መምጣቱን የጠቆሙት ተወካዩ ሁሉም የመንግሥትና የግል ተቋማት በጥንቃቄና በአግባቡ ማስወገድ እንዲችሉ አሠራር ይዘረጋልም ብለዋል።
የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ማደስንና መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልን መልመድ ይገባል ሲሉም መክረዋል።
የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻ፣ ከጨረር አመንጪ መሳሪያዎች ውጭ ሁሉም ዓይነት የተጣለ የኤሌክትሪክና የኤሌክትሮኒክ መሳሪያ እና የመሳሪያ ክፍል የሚያጠቃልል ነው።
በዚህም መሰረት ከሦስት ዓመታት በፊት በተካሄደ ጥናት በኢትዮጵያ 43 ሺህ ቶን የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ ክምችት መኖሩ ተመላክቷል።