አዲስ የሚወጡና የሚሻሻሉ አዋጆች በልዩ ጥንቃቄ ታይተውና ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው የሚጸድቁ ናቸው- የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ)፦ አዲስ የሚወጡና የሚሻሻሉ አዋጆች በልዩ ጥንቃቄ ታይተውና ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው የሚጸድቁ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

በምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ፤ በምክር ቤቱ የህግ ማርቀቅና ማጽደቅ ሂደት ሰፊና ጥልቅ የአሰራር ሂደቶችን የተከተለ መሆኑን ገልጸዋል። 

ለምክር ቤቱ በሚቀርቡ ረቂቅ ህጎች ዙሪያ የመንግስት ተጠሪ በኩል ለምክር ቤት አባላት ሰፊ ገለፃና ማብራሪያ የሚሰጥ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴው ረቂቅ ህጎች በዝርዝር እንዲፈትሹ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዝርዝር እይታ የተመራላቸው ቋሚ ኮሚቴዎችም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በረቂቅ ህጉ ላይ ጥልቅ ውይይት የሚያደርጉበት አሰራር መሆኑን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

ከህገ-መንግስቱና ከዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ጋር እንዳይጣረሱ በልዩ ልዩ መንገዶች የማጣራት ስራ የሚከናወን መሆኑንም አስረድተዋል።

በመሆኑም እነዚህን አሰራሮች በተከተለ መልኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለምክር ቤቱ ከቀረቡ 52 አዋጆች መካከል 42ቱ መጽደቃቸውን ጠቁመዋል።

ለዚህም የባለድርሻ አካላትና በረቂቅ አዋጁ ላይ ይመለከተኛል የሚሉ ግለሰቦች በነጻነት እንዲሳተፉ የህዝብ ተሳትፎ መድረኮች  እንደሚመቻቹ ነው ያብራሩት።

በምክር ቤቱ አዲስ የሚወጡም ሆኑ የሚሻሻሉ አዋጆች ሀገርና ህዝብን የሚጠቅሙና ለረጅም ዓመታት የሚያገለግሉ በመሆናቸው በልዩ ጥንቃቄ ታይቶ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው የሚጸድቁ መሆኑን ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በቀጣይም በሚያወጣቸው ህጎች ተፈጻሚነት ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ የመፈተሽ ስራ የሚሰራ ክፍል እንደሚያደራጅ ተናግረዋል።

በምክር ቤቱ የሚወጡ ህጎች የታለመላቸውን ዓላማ እንዲመቱ የእያንዳንዱ ዜጋ ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም