በክልሉ መገናኛ ብዙሃን ለልማትና ለሰላም ግንባታ ያላቸውን አስተዋጽኦ ከግምት ያስገባ የተቋማቱ ተደራሽነት ይጠናከራል

ሚዛን አማን ፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መገናኛ ብዙሃን ለልማትና ለሰላም ግንባታ ያላቸውን አስተዋጽኦ ከግምት ያስገባ የተቋማቱ ተደራሽነት እንደሚጠናከር የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የደቡብ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ማሻ ቅርንጫፍ ጣቢያን ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።

 

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ መገናኛ ብዙሃን ሕዝብና መንግስትን ድልድይ ሆኖ በማገናኘት ምትክ የለሽ ሚና ስላለው አገልግሎቱን ለማስፋፋት የክልሉ መንግሥት አበክሮ እየሰራ ይገኛል።

በተለይ መገናኛ ብዙሃን ለልማትና ለሰላም ግንባታ ያላቸውን አስተዋጽናኦ የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያስጠብቅ በመሆኑ የሚዲያ ተቋማትን ተደራሽነትን የማጠናከር ስራን የክልሉ መንግሥት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በሸካ ዞን የተከፈተው ጣቢያም የዚሁ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን አስረድተዋል።

የክልሉ ሚዲያ ኔትዎርክ መቋቋሙን ጠቅሰው በክልሉ ውስጥ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንን በቴክኖሎጂ ለማብቃት ጥረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

መገናኛ ብዙሃን ባሉበት አካባቢ ብቻ ሳይገደቡ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተደራሽነታቸው እንዲጎላ አስፈላጊውን ግብዓት እና የሰው ኃይል በማሟላት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በክልሉ ውስጥ እየሠሩ ያሉ መገናኛ ብዙሃን የቱሪዝም ሀብትን በማስተዋወቅና መልካም እሴቶችን በማጉላት የሕዝቦችን አብሮነት በሚያጠናክር መልኩ እንዲሠሩም አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን ኅብረተሰቡ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ወደ ኢኮኖሚ መቀየር የሚችልበትን መንገድ ማመላከት ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ የመልካም አስተዳደር እጥረቶችን ተከታትለው በመዘገብ ችግር ፈቺ ተቋም ለመሆን ጥረት ማድረግና የአካባቢውን የመለወጥ ተስፋን ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የማሻ ራዲዮ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምሩ ጎዱ ከክልሉ መንግስት በተገኘ የ25 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የስቱዲዮ ግብዓት በሟሟላት በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት መጀመር መቻሉን ጠቅሰዋል።

ዛሬ የተመረቀው የማሻ ኤፍ ኤም 103 ነጥብ 8 ራዲዮ ጣቢያ አማርኛን ጨምሮ በሸካ ዞን ውስጥ ባሉ የሸክኛ እና መዠንግርኛ ቋንቋዎች መረጃን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንደሚያደርጉም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም