ኮሌጁ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮሌጁ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ ነው
ጎንደር፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ)፦ የጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ክህሎት መር የስልጠና ስትራቴጂን በመከተል የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ መሆኑን ገለፀ፡፡
ኮሌጁ በ10 የሙያ ዘርፎች ከደረጃ አንድ እስከ አምስት ያሰለጠናቸውን 822 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡
የኮሌጁ ዲን አቶ ተስፋሁን መኮንን እንደተናገሩት፤ ኮሌጁ የአምራች ኢንዱስትሪውን የሰው ሃይል ፍላጎት በማጥናት በእውቀትና በክህሎት የበቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ለዘርፉ እድገት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
ኮሌጁ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በማጠናከርና በጥናት ላይ የተመሰረተ ክህሎት መር የስልጠና ስትራቴጂን በመተግበር የዘርፉን የሰው ሃይል ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለማሟላት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የቴክኖሎጂ ሸግግር ለማሳለጥም በዘርፉ የላቀ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸውን የሰለጠኑ ባለሙያዎች በማፍራት የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በ12 ሚሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ ወርክሾፖችን ከማቋቋም ጀምሮ የካይዘን ፍልስፍናን በመተግበር የቴክኖሎጂ ዕድገት የሚያፋጥን የሰልጣኞች የምዘና ስርዓት በማዘጋጀት እየተገበረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የአገልግሎት ዘርፉን የሰው ሃይል ፍላጎት ለማሳካትም 3ሺ ለሚጠጉ ስራ ፈላጊዎች አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት የስራ እድል ትስስር እንዲፈጠርላቸው ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ለምረቃ ከበቁት መካከልም 322ቱ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ሁሉም ተመራቂዎች የስራ ብቃት ምዘና ወስደው በአጥጋቢ ውጤት ያለፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ሁንዓለም አሻግሬ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች በቀሰሙት ሙያ ስራ ፈጣሪ በመሆን ሀገርና ህዝብን ለማገልገል ራሳቸውን ከወዲሁ ሊያዘጋጁ ይገባል ብለዋል፡፡
የሙያ ባለቤት መሆን የወጣቶች የመጀመሪያው የህይወት ምዕራፍ መሸጋገሪያ ድልድይ መሆኑን ጠቁመው፤ ተመራቂዎች በሰለጠኑበት ሙያ ስራ ፈጥረው ራሳቸውንና ሀገራቸውን በሚጠቅም ስራ እንዲሰማሩ የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደማይለያቸው ገልጸዋል፡፡
በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሀገራችን የጀመረችውን የቴክኖሎጂ መርሃ ግብር ለመቀላቀል ጽኑ ፍላጎት አለኝ ያለው በኤሌክትሮኒክስ የሙያ ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ተመራቂ አማረ ጌታነህ ነው፡፡
ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ሌላኛዋ ተመራቂ በለጡ ሙሉዓለም በበኩሏ፤ መንግስት ከተሞችን ዘመናዊ ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ የጀመረውን ንቅናቄ በሰለጠነችበት የቅየሳ ሙያ ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች፡፡
የጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያና በመካከለኛ ደረጃ የሙያ ስልጠና ዘርፍ ከ3 ሺ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡