ከንቲባ አዳነች አቤቤ መንግስት በቅርቡ ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ ዙሪያ ከንግድ ማህበረሰብ አባላት እና ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት በቅርቡ ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ ዙሪያ ከንግድ ማህበረሰብ አባላት እና ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ ከንግድ ማህበረሰብ አባላት እና ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር የፋይናንስ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በተገኙበት መንግስት በቅርቡ ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ ዙሪያ ውይይት አድርገናል ብለዋል።


 

ሪፎርሙ ለሀገራችን በርካታ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑንም በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።

በዋነኛነት ዘላቂ ልማትንና አካታችነትን ለማረጋገጥ፣ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ስርዓት ለመገንባት፣ የመንግስትን የእዳ ጫና ለመቀነስ፣ የተረጋጋ ተወዳዳሪ እና የዋጋ ግሽበትን መቀነስ የሚያስችል የገበያ ሁኔታን ለመፍጠር፣ ተኪ ምርቶችን በማምረትና ለውጪ ገበያ የምንልከውን ምርት በማሳደግ እንዲሁም ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በመፍጠር የውጪ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ወቅታዊ ተግዳሮቶችን ለመቆጣጠር ደሃው እና ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ እንዳይጎዳ የመንግስት ሰራተኞችን ደሞዝ መጨመር፣ ደሃውን መደጎም ፣ በተለይም በሴፍቲኔት የታቀፉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ገቢ በሚያስገኝና ተረጂነትን በሚቀንስ መንገድ መደገፍ እንዲሁም የስራ እድልን በስፋት መፍጠርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚተገበር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ከአምራቾች እና አስመጪዎች ጋር በቅርበት በመስራትና ገበያውን የሚያዛቡ፣ በተለይም ምንም ከውጪ ምንዛሪ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ምርቶች ላይ አላግባብ ዋጋ በሚጨምሩ እና ምርት በሚሰውሩ አካላት ላይ ጠንካራ የሆነ ቁጥጥር እና ህግ የማስከበር ስራ የምንሰራ ይሆናል ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም