ክረምቱ ለሰዎች አለን የምንልበትና በጎ ነገር የምንሰራበት መሆን አለበት - ዶክተር መቅደስ ዳባ

አሶሳ፣ ሐምሌ 28/2016 (ኢዜአ)፦  የክረምቱ ወራት ለሰዎች አለን የምንልበትና በጎ ነገር የምንሰራበት መሆን አለበት ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ አስታወቁ።

ዛሬ በአሶሳ ተገኝተው የበጎ ፈቃድ ሥራውን ያስጀመሩት የጤና  ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች በክልሉ ከ25 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተመላክቷል።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በደም ልገሳ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ነፃ ምርመራ፣ የቤት እድሳት እና በአረንጓዴ አሻራ እንደሚተገበርም ሚንስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ከዚሁ ጎን ለጎን 500 ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍም አድርጓል።

የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የአመራር አባላቱ የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣት ሂደትንም ጎብኝተዋል።

ሚኒስቴሩ በክልሉ የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል ድጋፍ እንደሚያደርግም ዶክተር መቅደስ ገልጸዋል።

ይህንን አብነት ወስዶ ሎሎቹም የበጎ ፈቃድ ሥራውን ማጠናከር እንዳለባቸው ያስታወቁት ሚኒስትሯ፤ በተለይም የክረምቱ ወራት ለሰዎች አለን የምንልበትና በጎ ነገር የምንሰራበት መሆን አለበት ብለዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲሊ ሐሰን ሚኒስቴሩ ባለፉት ዓመታት የጤና ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ወልተጂ በጋሎ በበኩላቸው የተጀመረውን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።


 

ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎቹ በአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና መስጫ ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሲሆን፤ በሆስፒታሉ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም