የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል - ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 28/2016 (ኢዜአ)፡-  የአስተዳደሩ ፖሊስ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ የጀመራቸውን አበረታች ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ  የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር አሳሰቡ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ  መምሪያ ለ14ኛ ጊዜ በሰላም ማስከበር የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያሰለጠናቸውን ፖሊሶች ዛሬ አስመርቋል ።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በስነ ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት የስራ መመሪያ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በአስተዳደሩ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ  እንዲሰፍን አበረታች ተግባራት አከናውኗል ።

የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ በመቀጠልና ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን በመጠበቅ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን ኃላፊነቱን በትጋት እንዲወጣ  አሳስበዋል።

ተመራቂ  ፖሊሶችም በቀሰሙት ሙያዊ ዕውቀት በመታገዝ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ በማስጠበቅ ሃላፊነታቸውን በትጋት እንዲወጡ አስገንዝበዋል ።

ለስልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረገው በሰላም ማስከበር የሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ምስጋና አቅርበዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ፖሊስ የሚመራበትን ዶክትሪን በመንደፍ የተከናወኑ የሰላምና የፀጥታ ማስፈን ስራዎች አበረታች ውጤቶች አስገኝተዋል ብለዋል።


 

ፖሊስ በተገበረው ሪፎርም በዘመናዊ አሠራርና አደረጃጀት እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዙ ስራዎች ማከናወኑን ጠቅሰው እነዚህ ተግባራት የድሬዳዋ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከልነት እንዲረጋገጥ መሠረታዊ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን አመልክተዋል።

የህግ የበላይነትን፤ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ ለማስከበር የተጀመሩ አበረታች የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል ።

ተመራቂ ፖሊሶች የተጀመሩትን ውጤታማ ስራዎች ወደ ላቀ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግሩም አስታውቀዋል።

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና  የህዝብን ሰላምና ፀጥታ  ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እተጋለሁ ያሉት ደግሞ በላቀ ውጤት የተመረቁት ኮንስታብል ሳምሶን እሼቱ ናቸው ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈቲህያ አደን ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ  የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ለስልጠናው መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ተቋማትና ግለሰቦች የተዘጋጀውን ሽልማትና ምስክር ወረቀት አበርክተዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ በሰላም ማስከበር የሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ፣ ወታደራዊ መኮንኖች፣ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ፣ ዑጋዞችና አባገዳዎች እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም