የተለያዩ የጥቆማ ዜዴዎችን ጨምሮ ነፃ የስልክ መሥመሮችን በመጠቀም ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ዘላቂነት ያለው ህጋዊ እርምጃ እንወስዳለን- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ)፦ የተለያዩ የጥቆማ ዜዴዎችን ጨምሮ ነፃ የስልክ መሥመሮችን በመጠቀም ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ዘላቂነት ያለው ህጋዊ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) የአዲስ አበባ ከተማን የንግድ ማህበረሰብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊነት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።


 

በውይይቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) መንግስት በተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ አስፈላጊነት እና አተገባበር ዙሪያ ለንግዱ ማህበረሰብ እና ለከተማው አመራር ግንዛቤ አስጨብጠዋል::

በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በቀረበው ግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ ያላቸውን ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ህገወጥ ንግድ የኢኮኖሚ ጤንነትን በማቃወስ ሀገርን ለአደጋ የሚዳርግ መሆኑን በመጥቀስ መንግሥት በህገወጥ ነጋዴዎች እና ከእነሱ ጋር በመተባበር ሀገርን በሚጎዱ ስግብግብ አመራሮችና ባለሞያዎች ላይ ህጋዊ እርምጃዎችን ቀጣይነት ባለው አግባብ እንዲወስድ ጠይቀዋል።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተሳታፊዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የሪፎርሙ ተግባራዊነት ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ በህጋዊነት ስራውን እየሰራ መሆኑን በማድነቅ ዶላር ጨመረ በሚል ሽፋን ያላአግባብ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ያሉት ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ የከተማ አስተዳደሩ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተናግረዋል።

ለሀገራችን ኢኮኖሚ ፍቱን መፍትሄ ይዞ የመጣውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ባልተገባ ሁኔታ በመተርጎም ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 250 በላይ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ለታዳሚዎቹ ገልፀዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ላይ ክትትሉና የእርምት እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በበኩላቸው የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚጨምር መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ለዚህም ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ህብረተሰቡ እስካሁን እያደረገ ላለው ውጤታማ ትብብር በማመስገን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዘላቂነት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም