የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል ሲያካሂድ የቆየውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ዛሬ አጠናቀቀ

ጋምቤላ፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል ሲያካሂድ የቆየውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ዛሬ አጠናቀቀ።

ተሳታፊዎች በቆይታቸው ለሀገር ይበጃሉ ያሏቸውን አጀንዳዎች በማሰበሳብ በመረጧቸው ኮሚቴዎች  አማካኝነት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በአደራ አስረክበዋል ።

የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት በክልሉ ካለፈው ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰበሳብ ሂደት ዛሬ በስኬት ተጠናቋል።


 

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለኢትዮጵያ  ዘላቂ ሰላምና መፃኢ እድል ይበጃሉ ያሏቸውን ሃሳቦች በነፃነት በማዋጣት ረገድ መልካም ተሳትፎ የታየበት ነበር ብለዋል።

ተሳታፊዎች ለህዝብና ለሀገር ይጠቅማሉ ያሏቸውን አጀንዳዎች በመለየትና በማሰባሰብ ረገድ ላሳዩት የነቃ ተሳትፎም ኮሚሽኑ ከፍተኛ ምስጋና እንዳለው ገልጸዋል። 

እንዲሁም በክልሉ ለአንድ ሳምንት ያህል ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ያለምንም ችግር በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ተባባሪ አካላት ሁሉ ኮሚሽኑ የላቀ ምስጋና እንዳለው  ኮሚሽነር መላኩ ተናግረዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ ያሉባትን ችግሮች በውይይት የምትፈታ ሀገር የሚለው ስም እንዲኖራት ለሀገር ዘላቂ ሰላም የጀመሩትን ፋና ወጊ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኮሚሽነር መላኩ ጠይቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም