በሸካ ዞን ከ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተገነባ ሆስፒታል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

ሚዛን ፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ)፦  በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሸካ ዞን ከ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ሆስፒታሉን መርቀው ከፍተዋል።

ኢንጂነር ነጋሽ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የክልሉ መንግስት ካለው በጀት አብዛኛውን በማኅበረሰብ ተኮር ልማት ላይ በማዋል የልማት ጥያቄዎችን ለመመለሰ እየሠራ ነው።


 

ዛሬ የተመረቀው የማሻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የዚሁ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ያልተሟሉ የውስጥ ግብዓቶችን በማሟላት የተቀላጠፈ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ሌሎች የልማት አውታሮችን ለመዘርጋት ክልሉ በቅርበት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል። 

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ሆስፒታሉ ከክልሉ መንግስት በተመደበ ከ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መገንባቱን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ክልሉ ለሆስፒታሉ የትራንፎርመር ግዢ ሦስት ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ጠቁመዋል። 

ሆስፒታሉ በዞኑ ለሚገኙ ከ150 ሺህ ለሚልቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ለአጎራባች ዞኖች ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥም አስረድተዋል።

የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው የሆስፒታሉ መገንባት የማሻ እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጥያቄ የመለሰ ነው ብለዋል።

የማሻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የግንባታ ሂደት በ2008 የተጀመረ ቢሆንም ሳይጠናቀቅ በመቋረጡ የሕዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱም በወቅቱ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም