የኢትዮጵያ ቡና ከምርት እስከ ግብይት ባለው ሂደት ለቱሪዝም ዘርፉ መጎልበት ትልቅ ሚና ይኖረዋል- ዶክተር አዱኛ ደበላ

ጅማ ፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቡና ከምርት እስከ ግብይት ባለው ሂደት የአገርን ገፅታ በመገንባት ለቱሪዝም ዘርፉ መጎልበት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር ) ገለፁ።

ቡናን ከቱሪዝሙ ዘርፍ ጋር በማስተሳሰር የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ያለመ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድን የቡናና ሻይ ባለስልጣን እና የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ዛሬ ተፈራርመዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ የቡና ዝርያዎችን በምርምር በማግኘት ምርቱን በማሳደግ እና የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

ቡናን ከማስተዋወቅም ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፉም ትልቅ ሚና እንዲኖረውና ትስስሩን እንዲጠናከር የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑንም በስምምነቱ ወቅት ተነስቷል።

የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር ) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ቡናን በጥራት ተመርቶና እሴት ተጨምሮበት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር የማስተሳሰር ሥራ ይሰራል።

''የቡና ምርትን በምርምር ማዕከሎች፣ በቡና ተክል ልማት ውስጥ ሎጆችን እና መዝናኛ ስፍራዎችን በመገንባት የቱሪስት መስህብ ይደረጋል'' ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ከቡና ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ በላይ ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ እንደተናገሩት፤  ከቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በመቀናጀት በክልሉ ያለውን የቡና ምርት ለዓለም በማስተዋወቅ፣ የቡናን ባህላዊ እሴት በማጉላት የቱሪስት መስህብ ይደረጋል።

ቡናን ጥሬውን ከመላክ ይልቅ እሴት ታክሎበት ቢላክ የተሻለ ገቢ ከማምጣቱም በላይ በማሸጊያው ላይ የኢትዮጵያን ባህላዊና ታሪካዊ ሀብት ለማስተዋወቅም ያግዛል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም