በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከመደገፍ ባሻገር የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነታችንን በትኩረት እንወጣለን- የሐረር ከተማ ነዋሪዎች

ሐረር፤ ሐምሌ 28/2016 (ኢዜአ)፡- በክልሉ የተጀመሩ የልማት ተግባራትን በተለያዩ አግባቦች ከመደገፍ ባሻገር እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነታቸውን በትኩረት እንደሚወጡ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

በክልሉ  በ2017  በጀት ዓመት በህዝብ ንቅናቄ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት ዙሪያ ከሐረር ከተማ ነዋሪዎች ጋር የውይይት መድረክ ተካሄዷል።

በመድረኩ የተገኙ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ በክልሉ የተጀመሩ የልማት ተግባራትን ከመደገፍ ባለፈ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነታችንን በትኩረት እንወጣለን።

ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ አሰፋ ፍስሃ በክልሉ በተከናወነውና በተመለከትነው የኮሪደር የልማት ስራ ሁላችንም ደስ ብሎናል ኮርተናልም ብለዋል።

በተለይ የክልሉ መንግስት በ2017 በጀት ዓመት በኮሪደር ልማትም ይሁን በማንኛውም ዘርፍ ለሚያከናውነው የልማት ስራ  ያላቸውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር እና ሌሎች የልማት ስራዎች ከተማዋ ውብ ገጽታ እንድትላበስ እያደረጉ ይገኛሉ ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ኢፍቱ ተስፋዬ ናቸው።

ሐረርን ውብ ጽዱና ለጎብኚውና ለነዋሪዎቿ ማራኪ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን ህዝቡ በባለቤትነት ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ይገባል ብለዋል።

በክልሉ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ እጅግ ማራኪና አስደሳች ነው ያሉት ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አብዲ ረሺድ ናቸው።

ለስኬታማነቱም የክልሉ መንግስትና አመራሩ የወሰደው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን የተናገሩት አቶ አብዲ የልማት ስራዎቹን ልንደግፍና ልናግዝ ይገባል ብለዋል።

መድረኩን የመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው በክልሉ አበረታች ስራዎች ቢከናወኑም በቂ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በተለይ ሐረርን የሚመጥኑ፣ ነዋሪዎቿን ይበልጥ ተጠቃሚ  የሚያደርጉና ፍትሃዊነት የተላበሱ ስራዎች በቀጣይ እንደሚከናወኑም አረጋግጠዋል።

በውይይት መድረኩ ላይም በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አመራር አባላት፣ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ ነዋሪዎችና ሌሎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም