የልማት ማህበሩ በድሬዳዋ ልማት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያሳድግ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል- ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ)፦ የስልጤ ልማት ማህበር በድሬዳዋ በተጀመሩ የልማት ተግባራት ላይ እያበረከተ የሚገኘውን አስተዋፅኦ እንዲያሳድግ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ገለፁ።

በድሬዳዋና አካባቢው የሚገኘው የስልጤ ልማት ማህበር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት "በአዲስ ተስፋ ሰላምን እናጠናክር" በሚል መሪ ሃሳብ ኮንፈረንስ ዛሬ በድሬዳዋ አካሄዷል። 


 

ከንቲባ ከድር ጁሃር በኮንፈረንሱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ ማህበረሰቡ በሚያከናውናቸው የልማት ተግባራት ከተረጂነት ለመውጣት ለተጀመረው ጥረት መሳካት በአብነት የሚጠቀስ ነው። 

በድሬዳዋ የሚኖሩ የማህበረሰቡ አባላት ከአስተዳደሩ ጎን በመቆም በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችና የበጎ ፍቃድ ልማት ስራዎች ላይ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ማህበሩ በድሬዳዋ በተጀመሩ የልማት ተግባራት ላይ እያበረከተ የሚገኘውን አስተዋፅኦ እንዲያሳድግ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ  አብራርተዋል።


 

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የስልጤ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አሊ ከድር በበኩላቸው፤ 22ተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ማህበሩ በአገር ዘላቂ ልማት ላይ የድርሻውን እያበረከተ ይገኛል። 

ማህበሩ ከአባላትና አጋሮች በሚያገኘው ሃብት፣ ዕውቀትና ጉልበት የዞኑን ህብረተሰብ ማህበራዊ ችግሮችን በማቃለል ረገድ አበረታች ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል ። 

የማህበረሰቡ ቋንቋ፣ ባህል እና ትውፊቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግም የራሱን ሚና እየተጫወተ መሆኑን አውስተዋል። 

የዛሬው ህዝባዊ ንቅናቄ መድረክ ዓላማም እነዚህን ስራዎች ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እና ከድሬዳዋ ልማት ማህበር ጋር በመቀናጀት በአስተዳደሩ የልማት አጋርነትን ለማፅናት መሆኑንም ገልጸዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም