ከተማዋን ውብና ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ስራዎች በግልና በመንግስት ተቋማትም በመስፋፋት ላይ ይገኛሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ):- አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ እንደ ከተማ አስተዳደር ከተጀመሩት የኮሪደር ልማት ስራዎች በተጨማሪ ስራው በሌሎች የግል እና የመንግስት ተቋማትም በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ::

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለሕዝብ መዝናኛ አገልግሎት እንዲውል የተገነባውን ፋውንቴይን መርቀው አስጀምረዋል::


 

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ከተማችን አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ እንዲሁም ለኑሮ ምቹ ለማድረግ እንደ ከተማ አስተዳደር ከጀመርናቸው የኮሪደር ልማት ስራዎች በተጨማሪ ስራው በሌሎች የግል እና የመንግስት ተቋማት በመስፋፋት ላይ ይገኛል ሲሉ አስፍረዋል::

በዛሬው ምሽትም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን (ኢኮስኮ) በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለሕዝብ መዝናኛ አገልግሎት እንዲውል የገነባውን ፋውንቴይን መርቀን አገልግሎት አስጀምረናል ብለዋል ::


 

ፒያሳ ዶሮ ማነቂያ አካባቢ በብራዘርስ ኮንስትራክሽን እና ቦሌ ሩዋንዳ ድልድይ ስር በአሰር ኮንስትራክሽን በተመሳሳይ ለሕዝብ መዝናኛ እንዲውሉ በራሳቸው ወጪ የገነቧቸውን ፋውንቴኖች ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል::

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን(ኢኮስኮ) ፣ብራዘርስ ኮንስትራክሽን እና አሰር ኮንስትራክሽን ከልብ እያመሰገንኩ ሌሎች የግል እና የመንግስት ተቋማትም ከዚህ ልምድ በመውሰድ አካባቢያቸውን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ላቀርብ እወዳለሁ ብለዋል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም