ተጠባቂው የ5 ሺህ ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ዛሬ ማምሻውን ይካሄዳል 

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦በፈረንሳይ ፓሪስ እየተካሄደ በሚገኘው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች የሚደረገውን የፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያውያን በጉጉት ይጠብቁታል።

ውድድሩ ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ15 ደቂቃ 80 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ስታድ ደ ፍራንስ ብሔራዊ ስታዲየም ይከናወናል።

በፍጻሜው አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ፣ አትሌት እጅጋየሁ ታዬና አትሌት መዲና ኢሳ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ። 

አትሌቶቹ ሐምሌ 26 ቀን 2016 ዓ.ም የተደረገውን ማጣሪያ አልፈው ለፍጻሜው ደርሰዋል።

ውድድሩን ያሸንፋሉ ተብሎ የቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል አንዷ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነችው ጉዳፍ ፀጋይ  ናት።

ጉዳፍ እ.አ.አ በ2023 በአሜሪካ ኢውጅን በተካሄደ ውድድር 14 ደቂቃ ከ00 ሴኮንድ ከ21 ማይክሮ ሴኮንድ ክብረ ወሰኑን የጨበጠችበት ሰዓት ነው።

አትሌቷ በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ5 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታ ነበር፤ በሁለተኛ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ወርቅ ለማምጣት ትሮጣለች።

ሌላኛዋ ተወዳዳሪ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ይሄ ሁለተኛ ተሳትፎዋ ነው።

እጅጋየሁ በ32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ5 ሺህ  ሜትር ፍጻሜ 5ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃ ነበር።

አትሌቷ እ.አ.አ በ2022 በአሜሪካ ኢውጅን በተደረገ ውድድር 14 ደቂቃ ከ12 ሴኮንድ ከ98 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።

በፍጻሜው ኢትዮጵያን የምትወክለው ሶስተኛ አትሌት ታዳጊዋ መዲና ኢሳ ናት፤ መዲና በኦሊምፒክ ስትሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

አትሌት መዲና ከሁለት ዓመት በፊት በለንደን በተካሄደ የዳይመንድ ሊግ ውድድር 14 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ ከ54 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።

በጋና አክራ በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም በተከናወነው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች እና ከሁለት ዓመት በፊት በኮሎምቢያ በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና በ5 ሺህ  ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

በፍጻሜው የኢትዮጵያ አትሌቶች ከኬንያውያኑ ፌዝ ኪፕዬጎንና ቢትሪስ ቺቤት እንዲሁም በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ ከሆነችው ሲፋን ሀሰን ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ በስፖርት ቤተሰቡ በጉጉት ይጠበቃል።

በተያያዘም ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ47 ደቂቃ ላይ የ8 መቶ  ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ይደረጋል፤ በውድድሩ ላይ አትሌት ፅጌ ዱጉማና አትሌት ወርቅነሽ መለሰ ይሳተፋሉ።

ትናንት በተደረገው የርቀቱ የግማሽ ፍጻሜ ውድድር አትሌት ፅጌ ከምድብ 2 1ኛ እንዲሁም ወርቅነሽ መለሰ በምድብ 1 2ኛ በመውጣት ለፍጻሜ አልፈዋል።

አትሌት ፅጌ 1 ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ ከ47 ማይክሮ ሴኮንድ፣ አትሌት ወርቅነሽ 1 ደቂቃ ከ58 ሴኮንድ ከ6 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓታቸው ነው።

አትሌቶቹ ትናንት በተደረገው ማጣሪያ በርቀቱ ያላቸውን የግል ምርጥ ሰዓታቸውን አሻሽለዋል፤ ወርቅነሽ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የግል ምርጥ ሰዓቷን ስታሻሽል ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

በተጨማሪም ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ4 ደቂቃ ላይ የ3 ሺህ ሜትር ወንዶች መሰናክል ማጣሪያ ውድድር ይካሄዳል፤ ለሜቻ ግርማ፣ ጌትነት ዋለና ሳሙኤል ፍሬው ይሳተፋሉ።

በ7 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው ለሜቻ ግርማ በማጣሪያው በምድብ 3 ይወዳደራል፤  በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በርቀቱ የብር ሜዳሊያ ማግኘቱ የሚታወስ ነው።

በምድብ 1 የሚገኘው አትሌት ጌትነት ዋለ 8 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ15 ማይክሮ ሴኮንድ እንዲሁም በምድብ 2 የሚወዳደረው አትሌት ሳሙኤል ፍሬው 8 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ78 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓታቸው ነው።

በሶስት ምድብ በሚደረገው ማጣሪያ ከየምድቡ ከአንድ እስከ አምስት የሚወጡ አትሌቶች ለፍጻሜው ያልፋሉ።

የፍጻሜው ውድድር ረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ43 ደቂቃ ላይ  ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እስካሁን ያገኘችው 1 የብር ሜዳሊያ ብቻ ነው፤ ሜዳሊያውን ያስገኘው አትሌት በሪሁ አረጋዊ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም