አዲስ በተገነቡና ተጠግነው ለአገልግሎት በበቁ የውሀ ተቋማት ተጠቃሚ ሆነናል - የላዕላይ ማይጨው ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ በተገነቡና ተጠግነው ለአገልግሎት በበቁ የውሀ ተቋማት ተጠቃሚ ሆነናል - የላዕላይ ማይጨው ወረዳ ነዋሪዎች
አክሱም ፤ ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል በላዕላይ ማይጨው ወረዳ አዲስ በተገነቡና ተጠግነው ለአገልግሎት በበቁ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የውሃ ተቋማቱ ለአገልግሎት መብቃት ንፁህ የመጠጥ ውሃን በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ከማገዙም በላይ ከተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች ተጋላጭነት እንደታደጋቸው ገልፀዋል።
በላዕላይ ማይጨው ወረዳ ደብረቃል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ወይዘሮ ማዕሾ ተወልደብርሃን እንደተናገሩት፤ በቀበሌው ላለፉት 15 ዓመታት ሲያገለግል የነበረው በእጅ የሚሰራ የውሃ ጉድጓድ ለብልሽት በመዳረጉ ለችግር ተጋልጠው ቆይተዋል።
ተበላሽቶ የቆየው የመጠጥ ውሃ ጉድጓድ ጥገና ተደርጎለት የተሟላ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።
በወረዳው የመዶገ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ተክለወይኒ መውጫ በበኩላቸው፤ ለብልሽት ተዳርጎ የቆየው የውሃ ጉድጓድ ተጠግኖና በውሃ ኬሚካል ታክሞ ንፅህናው እንዲጠበቅ በመደረጉ ንፁህ የመጠጥ ውሃን በአቅራቢያችን በማግኘት ተጠቃሚ ሆነናል ብለዋል።
ንጽህናው የተጠበቀ ውሃ በማግኘታቸውም ከውሃ ወለድ በሽታ ተጋላጭነት ነጻ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀበሌው ኩሒ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ውስጥ ለ500 አባወራዎችና እማወራዎች አገልግሎት የሚሰጥ የመጠጥ ውሃ ጉድጓድ በቂ ጥገና ተደርጎለት አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ንፅህናው የተጠበቀ ውሃ ተጠቃሚ ሆነናል' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አወጣሽ ተክለአብ ናቸው።
ጥገና የተደረገለትን የውሃ ጉድጓድ የአካባቢው ነዋሪ እንደሚጠብቀውና ሲበላሽም የመንግስት እጅ ሳይጠብቁ በራሳቸው ወጪ ለማሰራት በየወሩ ገንዘብ በማዋጣት በጋራ በተከፈተ የባንክ አካውንት እየቆጠቡ መሆኑን ገልፀዋል።
የቀበሌው ነዋሪ ወጣት አርሶ አደር ተመስገን በየነ በበኩሉ፤ የተገነቡት የውሃ ተቋማት ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ በእግር ተጉዘን ንፅህናው ያልተጠበቀ ውሃ ከወራጅ ወንዝ ቀድቶ ከመጠቀም ገላግለውናል ብሏል።
የቀበሌው ነዋሪዎች የተጠገኑና አዲስ የተሰሩ የውሃ ተቋማት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጿል።
በላዕላይ ማይጨው ወረዳ በ15 ገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የወረዳው አስተዳደር አመልክቷል።
በወረዳው መስተዳደር የመጠጥ ውሃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሙሉአለም መሰለ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በወረዳው በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖረውን ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ የውሃ ተቋማት ተገንብተዋል።
ከአገልግሎት ውጪ ሆነው የቆዩ 243 በእጅ የሚሳቡ የውሃ ጉድጓዶች ጥገና ተደርጎላቸው ለአገልግሎት በቅተዋል ብለዋል።
አዳዲስ በተገነቡና በተጠገኑ የውሃ ተቋማትም 210 ሺህ የሚሆን የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አስረድተዋል።
ለተቋማቱ ግንባታና ጥገና ሥራ ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን፤ በአራት ት/ቤቶች ውስጥም አዲስ የከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮና በእጅ ድጋፍ የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ መሳሪያዎች ተከላ መከናወኑንም ተናግረዋል።
ከአገልግሎት ውጭ የነበሩትን የውሃ መሰረተ ልማት የመጠገንና አዲስ የመጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ በመካሄዱም የወረዳው የመጠጥ ውሃ ሽፋን ከነበረበት 54 ከመቶ ወደ 57 ከመቶ ከፍ እንዲል እንዳስቻለውም አመልክተዋል።
በገጠር ቀበሌዎቹ የሚገኙ የመጠጥ ውሃ ተቋማትን የመንከባከብና የመጠበቁ ኃላፊነት የተጠቃሚው ህብረተሰብ በመሆኑ ተረክቦ እንዲያስተዳድረው ጭምር መሰጠቱን ገልፀዋል።
ለዚህ ተግባር እንዲያግዝም ህዝቡ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ማዋጣቱንም ተናግረዋል።