የሠላም ሚኒስቴር በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ የሠላም ሚኒስቴር በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የ36 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

በድጋፍ ርክክቡ ወቅት የሠላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም በገዜ ጎፋ ወረዳ የተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ እጅግ ልብ የሚሰብር በመሆኑ መላው የሀገራችን ህዝብ ማዘኑን ገልፀዋል።

ከአሁን በኃላ ከሐዘን ድባብ በመውጣት በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበው መላው ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ሐዘኑን ከመግለፅ ባሻገር ተጎጂዎችን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ፣ ጥራጥሬ እና አልባሳት ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።

በተጨማሪም በጥሬ ገንዘብ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ለሚደረገው ጥረት የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግም ቃል ገብቷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው በክልሉ ገዜ ጎፋ ወረዳ የህዝቡን ልብ የሠበረ አደጋ መከሰቱን ጠቁመው አደጋው ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሲያፅናና እና ሂደቱን በጥብቅ ሲከታተል መቆየቱን አስታውሰዋል።

በአካል በመምጣት እና ድጋፍ በማድረግ ለህዝቡ ያላቸውን አጋርነት በመግለፃቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ አመስግነዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እና ተጨማሪ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይፈጠር እንዲሁም የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የክልሉ መንግስት ከአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን እና ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ተጎጂዎች አስቸኳይ ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በሌላ ቦታ ለማስፈር የጥናት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አመላክተዋል።

አሁን ላይ ከአስቸኳይ ድጋፍ ባሻገር ተጎጂዎችን ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ሀብት የሚፈልግ በመሆኑ በቀጣይ ድጋፍ የሚያደረጉ እና መላው የሀገሪቱ ነዋሪዎች የገንዘብ፣ የቆርቆሮ እና የሚስማር ድጋፎች እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም