በሀዋሳ ከተማ ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተሰጠ

ሀዋሳ፤ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፡-በሀዋሳ ከተማ በማህበር ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለጠየቁ 1ሺህ 108 ለሚሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ቦታ ተሰጠ።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሃላፊ ኢንጂነር ምህረቱ ገብሬ ዛሬ በተዘጋጀው የቦታ ርክክብ መርኃ ግብር ላይ እንደገለፁት የቤት መስሪያ ቦታው የተሰጠው  በመኖሪያ ቤቶች ህብረት ስራ ለተደራጁ 35 ማህበራት ነው።


 

ማህበራቱ ተደራጅተው 50 በመቶ  የሆነውን ከ378 ሚሊዮን ብር በላይ ቆጥበው ያጠናቀቁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ የተሰጣቸው የመንግስት ሠራተኞች፤የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎች እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ናቸው ብለዋል።

ከቤት መስሪያ ቦታ ተጠቃሚዎች ውስጥ 334ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው ብለዋል።

ለመንግስት ሰራተኞቹ የተሰጠው ቦታ 51 ሺህ 950 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውና ባለ አራት ወለል ህንፃ መገንቢያ የሚሆን ነው ተብሏል።

ቦታው መሰጠቱ በነዋሪው ዘንድ ይነሳ የነበረውን የቤት ቅሬታና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ መኩሪያ መርሻዬ ናቸው።

ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪውን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ዘርፈ ብዙ ልማቶችን በመሥራት ላይ መሆኑንም ከንቲባው ገልጸዋል።

በመርኃ ግብሩ ላይ የከተማው አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የማህበራቱ አባላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም