የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 8ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ ማካሄድ ጀመረ

ድሬዳዋ፤ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፡-የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር  ቤት 3ኛ ዙር 3ኛ የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ ማካሄድ ጀመረ።

በጎፋ ዞን በደረሰው አደጋ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረው እና ለሁለት ቀናት የሚቆየው 8ኛ መደበኛ ጉባዔው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የሚመክር መሆኑን የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ከሪማ ዓሊ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በጉባዔው የአስፈፃሚውን እና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት እና በተያዘው በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ ተወያይቶ ያፀድቃል ተብሏል።

በተጨማሪም የምክር ቤት ፅህፈት ቤት እና ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች፣ የዋናው ኦዲተር እና የድሬዳዋ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የስራ አፈፃፀሞች ላይ ተወያይቶ የሚያፀድቅ መሆኑን የጉባዔው አጀንዳ ያመለክታል።

ከዚህ ባሻገር ምክር ቤቱ የድሬዳዋ አስተዳደር አስፈፃሚ እና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አካላትን እንደገና ለማቋቋም እና ተግባርና ኃላፊነታቸውን ለመወሰን በወጣ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባዔው የዘንድሮ በጀት ዓመት የበጀት ረቂቅ በማፅድቅ እና የተለያዩ ሹመቶችን እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ጉባዔው የድሬዳዋ ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የአስፈፃሚውን እና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለጉባዔው እያቀረቡ ይገኛል።

በ2000 ዓ.ም የተመሠረተው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 189 አባላት እንዳሉት ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም