በዞኑ ከ47 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ ሁለት ድልድዮች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደረጉ

ሚዛን አማን ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦  በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ከ47 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ ሁለት ድልድዮች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው ተገለፀ።

በሚዛን አማን ከተማ የተገነባው የአጉ ወንዝ ድልድይና በግዲ ቤንች ወረዳ የተገነባውን የዳማ ወንዝ ድልድይን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) መርቀው ከፍተዋል።


 

ለሁለቱ ድልድዮች 47 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የክልሉ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አብድዩ መኮንን ገልጸዋል።

የአጉ ወንዝ ድልድይ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር እና የሸኮ ወረዳን የሚያገናኝ ሲሆን የድልድዩ መገንባት በአካባቢው የሚመረቱ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች የግብርና ምርቶችን ወደ ገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።


 

42 ሜትር የሚረዝመው የዳማ ወንዝ ድልድይ የጊድ ቤንች እና የሰሜን ቤንች ወረዳዎችን ከማገናኘትም በተጨማሪ የጊድ ቤንች ወረዳን ከዞን ማዕከል ጋር የሚያገናኝ ወሳኝ ድልድይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም