የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የልማት ሥራዎች ከቻይና ድርጅት ጋር በትብብር ለመሥራት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የልማት ሥራዎች ከቻይና ድርጅት ጋር በትብብር ለመሥራት ተፈራረመ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የልማት ሥራዎች በትብብር ለመስራት ከቻይናው ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት ጋር ሥምምነት ተፈራርሟል።
ሥምምነቱን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የፋውንዴሽኑ ዳይሬክተር ይን ቼን ፈርመውታል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፤ ሥምምነቱ የተማሪዎች ምገባን ማስፋት፣ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የሶላር ታዳሽ ኃይልን ተደራሽ ማድረግና የንፁህ መጠጥ ውኃ እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፎችን ያካተተ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ ኅብረተሰቡን ከተረጂነት በማላቀቅ በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የፋውንዴሽኑ ዳይሬክተር ይን ቼን በበኩላቸው ላለፉት አስር ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ፋውንዴሽኑ በተጠቀሱት ዘርፎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።