በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በድሬዳዋ የህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ውጤቶች ተመዝግበዋል - ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በድሬዳዋ የህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ውጤቶች ተመዝግበዋል - ከንቲባ ከድር ጁሃር
ድሬዳዋ ፤ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፦በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የማህበራዊ እና የምጣኔ ሃብታዊ የልማት ውጤቶች መመዝገባቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ።
የድሬዳዋ አስተዳደር 3ኛ ዙር 3ኛ የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ነው ።
የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ለጉባኤው የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት የአስፈፃሚውን እና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዘርፎች የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
ከንቲባው በሪፖርታቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የገጠርና የከተማን ህዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የማህበራዊ እና የምጣኔ ሃብታዊ የልማት ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የፍትህ እና የፀጥታ አካላትን በማቀናጀት እና አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታን የማስፈን ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ በጤና፣ በትምህርት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ በመንገድ ግንባታ እና በሌሎች ዘርፎችም የህዝብን የዓመታት የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ያቃለሉ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ከንቲባ ከድር ማብራሪያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ የሚታየውን የስራ አጥነት ችግሮች ለማቃለል በተከናወኑ የተቀናጁ ስራዎች አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል።
በገጠርና በከተማ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ19ሺህ 660 በላይ ሰዎች ቋሚ የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ከ18ሺህ 80 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል በመፍጠር የዕቅዱን 91 ነጥብ 9 በመቶ ማሳካት መቻሉንም ተናግረዋል።
ቋሚ የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው በተጨማሪ 3ሺህ 800 የሚሆኑ ወጣቶችና ሴቶች በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ጊዜያዊ የስራ ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
እንደ ከንቲባ ከድር ገለፃ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገኙ የልማት ውጤቶችን በተሻለ መንገድ ለማስቀጠል የሚያስችል በድሬዳዋ ብሩህ እና የተረጋጋ የሥራ ምህዳር አለ።
በጉባዔው ላይ የተሳተፉ የድሬዳዋ አስተዳደር የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በገጠርና በከተማ ያካሄዱትን የክትትልና የቁጥጥር ምልከታዎችን መነሻ በማድረግ በቀረበው ሪፖርት ላይ አስተያየታቸውን አቅርበዋል።