በምዕራብ ሸዋ ዞን የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

አምቦ ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦  በምዕራብ ሸዋ ዞን ጨሊያ ወረዳ ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ 36 የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።

የልማት ፕሮጀክቶቹ ዛሬ ሲመረቁ የኦሮሚያ ክልል የአመራር አባላት፣ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ እና የወረዳ አመራሮች፣ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ነዋሪዎች ተገኝተዋል። 

ከተመረቁ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል ለጨሊያ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የሚያገለግል ህንጻ፣ መንገድ፣ የመጠጥ ውሃ ተቋማት፣ ድልድይ እና ሌሎች የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።


 

የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ዛሬ ለምረቃ የበቁትን ጨምሮ በአጠቃላይ በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የልማት ስራዎች ለአገልግሎት በቅተዋል።

አጠቃላይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁት 762 የተለያዩ ፕሮጀክቶች መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ 

የተጠናቀቁት የልማት ፕሮጀክቶች የዞኑ ህዝብ ለረጅም ጊዜ ሲጠይቃቸው የነበሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች መሆናቸውንም አስታውሰዋል።


 

ከለውጡ ወዲህ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ አጠናቆ ለአግልግሎት ከማብቃት አንጻር አበረታች እንቅስቃሴዎች እንዳሉም ተናግረዋል።

በፕሮጀክቶቹ ምረቃ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ሃላፊ አቶ ሞገስ ኢደኤ በበኩላቸው የዞኑ ነዋሪዎች ፕሮጀክቶቹ የራሳቸው መሆኑን ተገንዝበው እንክብካቤ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል፡፡

የጨሊያ ወረዳ ነዋሪዎች በበኩላቸው ለአገልግሎት የበቁ ፕሮጀክቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ስላላቸው ረጅም ዓመት እንዲያገለግሉ እንከባከባቸዋለን ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም