በኦሮሚያ ክልል በአርብቶ አደር አካባቢዎች የተከናወኑ የኩታገጠም የግብርና ልማት ሥራዎች ውጤታማ ናቸው 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/ 2016 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በአርብቶ አደር አካባቢዎች የተከናወኑ የኩታገጠም የግብርና ልማት ሥራዎች ውጤታማ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።  

በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የተመራው የክልሉና የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች  በምዕራብ ጉጂ ዞኖች የተከናወኑ የግብርና ሥራዎችን ጎብኝቷል።  

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ጊዜ፤ ባለፉት ዓመታት በአርብቶ አደር አካባቢ ከፍጆታ ባለፈ ገበያ  ተኮር የግብርና ልማት ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ገልፀዋል።


 

ኩታገጠም እርሻን ማስፋትን ጨምሮ ግብርናን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ረገድ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦትና የአጠቃቀም ባህልን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ለውጥ አምጥቷል ነው ያሉት።

በተለይም የሰብል ልማት በማይታወቅባቸው የክልሉ አካባቢዎች የተከናወኑ ተግባራት የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ምርት ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችና ለውጭ ገበያ እየቀረበ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይም በዘርፉ የተከናወኑ መልካም ተግባራትን በማስፋት ከግብርና ዘርፍ በርካታ ባለሃብቶችን የማፍራት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ይህም በዋነኝነት በአካባቢው ያሉትን ፀጋዎች ጥቅም ላይ በማዋል የሚገኝን ገቢ በመቆጠብ ኢንቨስትመንት ላይ በማዋል ሊሆን ይገባል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም