የመከላከያ ሠራዊት ለመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር የቁሳቁስ ድጋፍና ማዕድ አጋራ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሠራዊት ለመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር የቁሳቁስ ድጋፍና ማዕድ አጋራ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦የመከላከያ ሠራዊት ለመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር የቁሳቁስ ድጋፍና ማዕድ አጋራ።
በድጋፍና የማዕድ ማጋራት ሥነ-ሥርዓቱ የመከላከያ ሠራዊት የሥራ ኃላፊዎችና የሠራዊቱ አባላት ተገኝተዋል።
በመከላከያ ሠራዊት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ሁሉአገርሽ ድረስ እንደገለፁት፤ የመከላከያ ሠራዊት የአልባሳት፣ የንጽህና መጠበቂያና ሌሎችንም ድጋፍ አድርጓል።
የመከላከያ ሠራዊቱ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት በመሳተፍ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት የአገርና የሕዝብ ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ ለአረጋውያንና ለአቅመ ደካሞች ያለውን በማካፈልና በልማት ሥራዎች በመሳተፍ የሕዝብ ልጅ መሆኑን እያስመሰከረ እንደሆነ ገልፀዋል።
ሠራዊቱ በቀጣይ በሚችለው ሁሉ ለማኅበሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለጽ፤ ሌሎችም ለማኅበሩ ድጋፍ በማድረግ ወገናዊ አለኝታነታቸውን ማሳየት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት በማኅበሩ ታቅፈው የሚገኙ ወገኖችን በማሰብ የቁሳቁስ ድጋፍና ማዕድ በማጋራቱ አመስግነዋል።
ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች የመከላከያ ሠራዊቱን አርዓያ በመከተል ለማኅበሩ የሚችሉትን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።