የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የልማት ሥራዎች ከቻይና ድርጅት ጋር በትብብር ለመሥራት ተፈራረመ 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የልማት ሥራዎች ከቻይናው ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት ጋር በትብብር ለመሥራት ሥምምነት ተፈራረመ። 

ሥምምነቱን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የፋውንዴሽኑ ዳይሬክተር ይን ቼን ፈርመውታል።   

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ ስምምነቱ በሰባት ፕሮግራሞች የገጠር ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ ደሀና ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል። 


 

ሰባቱ ፕሮጀክቶች የሚተገበሩበት ጊዜ እንዳላቸው አንስተው፤ የተማሪዎች ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ዕቃዎቹ ወደብ ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል።

ድጋፉ ገንዘብ፣ ቴክኒክና ቴክኖሎጂን ያካተተ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ መሆኑንም ጠቁመዋል።  

የተማሪዎች ምገባን በተለያዩ ክልሎች ማስፋት፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት፣ በገጠር ለሚኖረው ማኅበረሰብ የሶላር ታዳሽ ኃይልን ተደራሽ ማድረግና የንጹህ መጠጥ ውኃ እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፎችን ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል። 

ፕሮጀክቶቹ ሕብረተሰቡን ከተረጂነት በማላቀቅ በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል። 

የቻይናው ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት በመጀመሪያ ዙር  320 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ የ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት መተግበሩንም ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ የፋውንዴሽኑ ዳይሬክተር ይን ቼን በበኩላቸው፤ ላለፉት አሥር ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ገልፀዋል።

ፋውንዴሽኑ በተጠቀሱት ዘርፎች አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም