''ምድረ ቀደምት'' የሚለው መጠሪያ ኢትዮጵያን በልክ ይገልጻታል - የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
''ምድረ ቀደምት'' የሚለው መጠሪያ ኢትዮጵያን በልክ ይገልጻታል - የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪዎች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ ''ምድረ ቀደምት'' የሚለው መጠሪያ ኢትዮጵያን በልክ ይገልጻታል ሲሉ ኢትዮጵያን የጎበኙ የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪዎች ተናገሩ።
የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘችበትን 50ኛ ዓመት በተለያዩ መርኃ-ግብሮች እየተዘከረ ሲሆን፤ በቅርቡም ከ34 አገራት የተውጣጡ ከ240 በላይ የዘርፉ ተመራማሪዎች በኢትዮጵያ ቆይታ ነበራቸው።
በቆይታቸውም የአድዋ መታሰቢያን፣ ብሔራዊ ቤተ-መዘክርና አንድነት ፓርክ ተዘዋውረው ጥንታዊ ቅርሶችና የቅሪተ-አካል ክምችቶችን ተመልክተዋል።
ኢዜአ ያነጋገራችው ጎብኚዎች፤ኢትዮጵያ በሰው ዘር ምንጭነቷ ብሎም በዳበረ ጥንታዊ ቀደምት ታሪኳ ምድረ ቀደምት የሚለው መጠሪዋ በልክ ይገልጻታል ብለዋል።
በአሜሪካ በሚገኘው ስቶክተን ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ሕይወት ትምህርት ክፍል ተመራማሪ ፕሮፌሰሯ ማርጋሬት ሌዊስ፤ከፈረንጆቹ አቆጣጠር 1997 ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአፋር አካባቢ ምርምሮችን አድርገዋል።
የምርምር ትኩረታቸውም ሉሲ በነበረችበት አካባቢ የነበሩ እንስሳት ላይ እንደሆነ የሚያነሱት ፕሮፌሰሯ፤ ኢትዮጵያን በብዙ መለኪያዎች ምድረ ቀደምት አገር እንደሆነች ያነሳሉ።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የቅድመ ሰው ዘርፈ-ቅሪተ-አካሎች ስለኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ስለመላው የሰው ልጆች የሚናገሩ እንደሆኑ ይገልጻሉ።
ሌላው የሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪ ታንዛኒያዊ ፕሮፌሰር ጃክሰን ጃው፤ በሥነ-ምድር ጥናት ቀደምትነት የጊዜ ዑደትና የዕድሜ ቅደም ተከተል አኳያ ኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ ናት ይላሉ።
ኢትዮጵያ እስከ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዕድሜ ያላቸው ቅሪተ-አካል የተገኘባት አገር መሆኗ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀደምት የሚያደርጋት ታሪኮች ባለቤትም እንደሆነ ተናግረዋል።
በእንግሊዙ ሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር አመጣጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ስፔናዊው ኢግናሲዮ ላሳጋባስተር (ዶ/ር)፤ የሉሲ ቅሪተ-አካል በኢትዮጵያ መገኘት እኔን ጨምሮ በርካታ ተመራማሪዎች በዘርፉ ጥናት እንዲሰማሩ አነቃቅቷል ይላሉ።
ብሔራዊ ሙዚየምን ጨምሮ የቅደመ ሰው ዘር አመጣጥና የኢትዮጵያን ታሪኮች የያዙ ተቋማት የተደራጁበትን መንገድ አድንቆ፤ ኢትዮጵያ በቅሪተ-አካሎች ብቻ ሳይሆን በሌሎች አርኪዮሎጂካል ዘርፎች ምድረ ቀደምት የምትገኝ ሀገር ናት ብለዋል።
በሌላ በኩል የታንዛኒያ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂስት ትምህርት ክፍል ባልደረባዋ ማሪየም ቡንዱላ (ዶ/ር) እና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዋ ኬንያዊት ርብቃ ሙሪዩኪ፤ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ያደራጀችበትን አግባብ አድንቀዋል።
ቅርስን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማሻገር ትውልዱ በታሪኩ እንዲኮራ ብቻ ሳይሆን ከትናንት ማንነቱ እንዲማርበት የሚያስችል እንደሆነም ገልፀዋል።
የ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ዓመት ዕድሜ ያላት የሰው ልጅ ቅሪተ-አካሏ ሉሲ ወይም ድንቅነሽ በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ኅዳር 24 ቀን 1974 በአፋር ክልል ''ሐዳር" የተባለ ሥፍራ ነበር የተገኘችው።