ክልሉ የኮሌራና የወባ በሽታዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ተግባር እየተከናወነ ነው 

ባህር ዳር፣ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የኮሌራና የወባ በሽታዎችን  ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው ያለፈው ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ የትውውቅ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

የቢሮ ኃላፊው አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተደረገው የተቀናጀ ጥረት በዘርፉ አበረታች ስራ ማከናወን ተችሏል።

በተለይም የኮሌራና የወባ በሽታዎችን ለመከላከል መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ በማዳረስ  ለመቆጣጠር ጥረት መደረጉን አውስተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም የኮሌራ በሽታ ስርጭትን ለመግታት ህብረተሰቡ የግልና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ ራሱን ከበሽታው እንዲከላከል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ 22 ወረዳዎች ላይም የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

አሁንም ተጨማሪ ርጭት ለማከናወን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተው፤ ህብረተሰቡ ለወባ በሽታ አጋላጭ የሆኑ ስፍራዎችን ማፅዳት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ገበያው አሻግሬ በበኩላቸው፤ በዞኑ የወባ በሽታን ለመከላከል  አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን የአልጋ አጎበር በማሰራጨትና ህብረተሰቡን በማስተባበር የመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በዘጠኝ ወረዳዎች የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭትና ህብረተሰቡን ከበሽታው መከላከል በሚቻልበት አግባብ ግንዛቤን የማሰራጨት ስራ እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመድረኩ ላይም የቢሮው፣ የዞንና የወረዳ የዘርፉ አመራሮች እንዲሁም አጋርና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም