በአማራ ክልል በምርት ዘመኑ  ለማምረት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ ነው 

ባህር ዳር ፤ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በ2016/2017 የምርት ዘመን ለማምረት በዕቅድ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በተቀናጀ አግባብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በገጠር ልማት ዘርፍ የተደራጁ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተካሂዷል። 

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤በምርት ዘመኑ ካለፈው ዓመት የተሻለ ለማምረት ትኩረት ተሰጥቷል።


 

እስካሁን በተደረገው  በዕቅድ ከተያዘው 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታሩ በተለያየ የሰብል ዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል።

በግብአት አቅርቦት በኩልም  ካለፉት ዓመታት በተሻለ እስከሁን 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን ተናግረዋል።

በክልሉ በምርት ዘመኑ ዕቅድ መሰረት ከሚለማው መሬት  169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማሳካት የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

''የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካትም ቀሪውን መሬት በዘር ከመሸፈን ባሻገር የለማውን ሰብል ከፀረ አረምና ፀረ ሰብል ተባይ የመከላከል ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው'' ብለዋል።

የዝናቡ ስርጭት ለሰብል ልማቱ ተስማሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ምርታማነትን በሄክታር ከ28 ነጥብ 2 ኩንታል ወደ 32 ነጥብ 7 ኩንታል ለማሳደግ የተሻሻሉ አሰራሮችን በመተግባር ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል። 


 

የክልሉ መንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለክልሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም ባለፈው በጀት ዓመት አንድ ሺህ 37 ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባት መቻሉን ገልጸዋል።

እንዲሁም 73 ድልድዮች መገንባታቸውንና  11ሺህ 902 ኪሎ ሜትር የነባር መንገዶች ጥገና ስራም መከናወኑንም አውስተዋል።

በያዝነው በጀት ዓመትም ካለፈው ዓመት በተሻለ የመንገድ ግንባታና የነባር መንገዶች ጥገና ስራ ለማከናወን መታቀዱን አስረድተዋል።


 

የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ  ማማሩ አያሌው(ዶ/ር) ናቸው።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 14 ከፍተኛ የውሃ ተቋማትን፣ 640 አነስተኛ የውሃ ተቋማትን በመገንባት ከ400 ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከ73 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 75 ነጥብ 1 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል።

በያዝነው የበጀት ዓመትም 14 ከፍተኛና መካከለኛ የውሃ ተቋማትን እንዲሁም  አንድ ሺህ 600 አነስተኛ የንፁህ መጠጥ  በመገንባት የመጠጥ ውሃ ሽፋኑን 77 ነጥብ 1 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል።

በዕቅድ ትውውቅ መድረኩ የክላስተር ተቋማት ከፍተኛ የአመራር አባላት፣ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎችና  የዞን ምክትል አስተዳዳሪዎች ተሳትፈዋል።    

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም