የሀዲያ ብሔረሰብ ባህላዊ የዳኝነትና የግጭት አፈታት ሥርዓት ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲሸጋገር እየተሰራ ነው

ሆሳዕና ፤ ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፡- የሀዲያ ብሔረሰብ ባህላዊ የዳኝነትና የግጭት አፈታት ሥርዓት ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲሸጋገር ለማስቻል በጥናት የተደገፉ ሥራዎች እየተከናወኑ  መሆኑን የሀዲያ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ የሌሞን ወረዳ ማህበረሰብን የሚወክሉ የበላይ ጠባቂ የሀገር ሽማግሌዎችን የመሰየም መርሃ ግብር ዛሬ በወረዳው ኃይሴ ቀበሌ ተካሂዷል። 

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ታምሬ ኤርሚያስ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በሀዲያ የአካባቢውን ሰላም የሚያስጠብቁና የማህበረሰቡን የእርስ በርስ ትስስር ለማጎልበት የሚጠቅሙ በርካታ ባህላዊ እሴቶች አሉ።


 

ህብረተሰቡ ግጭቶችን የሚያስወግድበትና ሰላም የሚያወርድበት ባህላዊ የዳኝነትና ግጭት መፍቻ ሥርአት ወይም የ"ጢጉላ ባህላዊ ግጭት አፈታት" ከባህላዊ እሴቶቹ አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሥርአቱ ግጭትን በሰለጠነ መንገድ በውይይት በመፍታት ሰላምን ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸው፣ ባህላዊ እሴቱ ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲተላለፍና ተሰንዶ እንዲቀመጥ ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የጥናት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቱ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ታምሬ፣ ስርዓቱን የሚመራው ሰውም በየጊዜው በህዝብ እየተመረጠ የስልጣን ሽግግር እንደሚደረግ ገልጸዋል።

አቶ ታምሬ እንዳሉት ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቱ ለዴሞክራሲ መጎልበት ጭምር ጉልህ ሚና አለው።

የሀድያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዳኛ ጥላሁን ዴታሞ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት በዘመናዊ ፍርድ ቤቶች ያለውን የሥራ ጫና ከማቃለል አንጻር አስተዋጾው የጎላ ነው።


 

ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቱ  እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላፍ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ባህል ሽማግሌ አቶ ታደሰ ኮራ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውና ዘመናትን ያስቆጠሩ በርካታ ባህላዊ ዕሴቶች እንዳሉ ገልጸዋል።


 

ግጭት በሰላማዊ መንገድ በውይይት የሚፈታባቸው ዕሴቶች ለሀገራዊ አንድነት እንደምሶሶ ናቸው ያሉት አቶ ታደሰ፣ ህብረተሰቡ ለዘመናት የተጠቀመባቸውን እነዚህን እሴቶች መጠበቅ ይገባናል ብለዋል።

የአብሮነት እሴቶቻችንን በዘመናዊነት ሳይበረዙ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በሚሰሩ ሥራዎች ውስጥ የአገር ባህል ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች ተቀራርበው በመስራት የሰላም እጦት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን መፍታት እንደሚችሉ የጠቆሙት አቶ ታደሰ፣ እሳቸውም የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

"ሰላምን ማስጠበቅ የሚጀመረው ከአካባቢ ነው።" ያሉት ደግሞ በሌሞ ማህበረሰብ ዘንድ በሰብሳቢ ዳኝነት የተመረጡት ዳኛ ብርሃኑ ጡሞሮ ናቸው።


 

የሀገር ሽማግሌዎች ጽንፍ ከመያዝና ከእኔነት አመለካከት ወጥተን ፍትሃዊ ፍርድ በመስጠት ለህዝብ ሰላምና አብሮነት መጠናክር ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል።

የሀዲያን አንድነት ከማስጠበቅ ባለፈ በአጎራባች አካባቢ ካሉ ህዝቦች ጋር አብሮነትን በማጠናከር ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና የባህል ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም