በአማራ ክልል የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በቅንጅት ይሰራል - ዶክተር አብዱ ሁሴን

ባህር ዳር፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በአዲሱ ዓመት የትምህርት ተደራሽነትን የበለጠ ለማስፋት በቅንጅት እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አብዱ ሁሴን ገለፁ።

በክልሉ የማህበራዊ ክላስተር አመራር አባላት የተሳተፉበት በትምህርት ጉዳዮች የሚመክር መድረክ በባህር ዳር እየተካሄደ ነው።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለፁት፤ የክልሉ መንግስት ባለፉት ዓመታት የመማሪያ መፃሀፍት፣ ወንበር፣ ጠረጴዛና ሌሎች ግብዓቶችን በማሟላት ለትምህርት ዘርፍ መጠናከር ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል።

በክልሉ የትምህርት ተደራሽነትን የበለጠ ለማስፋት ከተያዘው ክረምት ጀምሮ የሚፈፀም የትምህርት ንቅናቄ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

የክረምት የዝግጅት ስራዎችን ጥንካሬና ድክመት በመገምገም በአዲሱ ዓመት ከምዝገባ ጀምሮ በቅንጅት በመረባረብ የዘርፉን ዕቅድ ማሳካት ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ተናግረዋል።


 

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መኳንንት አደመ በበኩላቸው፤ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በቅድሚያ ነባርና አዲስ ተማሪዎችን በመለየት ከነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በንቅናቄ ምዝገባ ይከናወናል ብለዋል።

በተጨማሪም ትምህርት ቤቶችና የትምህርት ማህበረሰብ ያሉበት ሁኔታ በመለየት በግብዓት፣ ክህሎትና ሌሎች ስራዎች ለማጠናከር በየደረጃው ያለው ለትምህርት ዘርፉ አመራርና ባለድርሻ አካላት በልዩ ትኩረት ይሰራሉ።

በመድረኩ የማህበራዊ ክላስተር የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም