በቀሪዎቹ የክረምት ወራት ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጠበቃል 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ በቀሪዎቹ የክረምት ወራት የሚጠበቀው ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን ለግብርናና ለሌሎች ማኅበራዊ ሥራዎች ማዋል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።  

የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ የክረምት ወራት የዝናብ ሁኔታን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ በነሐሴና በመስከረም ወራት የክረምት ዝናብ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ይችላል ብለዋል። 

የክረምት ወቅት ዝናብ አወጣጥም በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብና በመካከለኛ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመዘግየት አዝማሚያ እንደሚኖርም ተናግረዋል።

የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች የትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ፣ ሀረሪ ክልልና ድሬዳዋ አስተዳደር፣ ሰሜን ሶማሌ ክልል አካባቢ ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ትንበያዎች ያሳያሉ ብለዋል።

ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት ከመደበኛ በላይ የሆነውን ዝናብ ለግብርናና ለሌሎች ማኅበራዊ ሥራዎች ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል። 

የሚኖረው ዝናብ ለመኽር ሰብሎች በቂ እርጥበት እንዲኖር የሚያስችል ሲሆን በእርጥበት አጠር አካባቢዎች የዝናብ ውኃን ለማሰባሰብ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በተጨማሪም የግድቦች የውኃ መጠንና የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ውኃ እንደሚጨምሩ እና ለአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።

በሌላ መልኩ የአፈር ውስጥ እርጥበት መብዛት የአፈር መሸርሸርና የመሬት መንሸራተት፣ የሰብል በሽታዎች ሊኖር ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።  

ጎን ለጎንም በማሳዎች ላይ የውኃ መተኛት በረባዳማ አካባቢዎች በሚዘሩ ሰብሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።  

የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችልና የወንዝ ሙላት ሊከስት ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም