በጌዴኦ ዞን የተጀመሩ የልማት ስራዎች መጠናከር  እንዳለባቸው ተገለጸ

ዲላ ፤ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፦ በጌዴኦ ዞን በተለያዩ ዘርፎች የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ  ተገለጸ።

የዞኑን ህዝብ የወከሉ የምክር ቤት አባላት በጌዴኦ ዞን በዲላ ዙሪያ ወረዳና በዲላ ከተማ በየዘርፉ  እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

ጉብኝቱም በዋናነት በግብርና ዘርፍ የቡና፣ የእንሰትና የፍራፍሬ ልማት፣  የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እንዲሁም የኮሪደር ልማት ስራዎችን ያካተተ ነው።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ ኮሬ በወቅቱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የቡና፣ የእንሰትና የፍራፍሬ ክላስተር ልማት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተስፋ ሰጭና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው።

በተለይ በጥቂት አርሶ አደሮች ማሳ የተጀመረው ኩታ ገጠም የቡና ልማትን ማስፋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።


 

ከአዲስ አበባ ከተማ ልምድ በመውሰድ በዲላ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ወደ ስራ መገባቱ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ተግባር መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት አባል አቶ ንጉሴ አሰፋ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በዞኑ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙና ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

በተለይ የዲላ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ግንባታ ለማጠናቀቅና ለአገልግሎት ለማብቃት የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥረቱን እንደሚያግዙም አረጋግጠዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፀሃይ ወራሳ በበኩላቸው፤ በዞኑ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ተስፋ ሰጪና የህብረተሰቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚመልሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የልማት ስራዎቹ ጅምራቸው መልካም መሆኑን አንስተው፤ የህዝቡን የልማት ፍላጎት እስኪመለስ ድረስ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ በበኩላቸው፤ በዞኑ በተለይ በምግብ ሰብል እራስን በመቻል ከተረጅነት ለመላቀቅ የኩታ ገጠም የግብርና ልማት ስራዎች ላይ በማተኮር በውስን ስፍራ ከፍተኛ የምርት መጠን እየተገኘ ነው ብለዋል።

በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ ቡና በሄክታር 19 ኩንታል ማግኘት መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ዋና አስተዳዳሪው እንደተናገሩት፤ የዞኑ የለውጥ ሂደት ከግብ እንዲደርስ በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላት  አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም