በአለርት ሆስፒታል የሕክምና መሳሪያዎች የሚታደሱበት ማዕከል ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ  

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ በአለርት ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና መሳሪያዎች የሚታደሱበት ማዕከል ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።   

የመሰረት ድንጋዩን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባና በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ አስቀምጠዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ጊዜ፤ እንደ አገር ያረጁ የሕክምና ግብዓቶችን መልሶ በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።   


 

በዚህም ምክንያት በርካታ የሕክምና መሣሪያዎች ታድሰው ዳግም አገልግሎት መስጠት እየቻሉ ለብክነት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰው ዛሬ ግንባታው የተጀመረው ማዕከል ያረጁ የሕክምና መሳሪያዎችን አያያዝና አጠቃቀምን የሚያሻሽል መሆኑን ገልጸዋል።    

ግንባታው በኮሪያው ሪፐብሊክ ዓለም አቀፍ የጤና እንክብካቤ ፋውንዴሽን (ኮፊ) በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄድ መሆኑን አመላክተው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተናግረዋል። 


 

ማዕከሉ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለጎረቤት አገራት ጭምር አገልግሎት ጭምር አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ እንደሚገነባ ተናግረዋል።   

በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ በበኩላቸው፤ ኮሪያ ሪፐብሊክና ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ናቸው ብለዋል።


 

ሁለቱ አገራት በተለያዩ የልማት መስኮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ማዕከል በኢትዮጵያ የሕክምና መሳሪያዎችን በማደስና ወደ ሥራ በማስገባት የአገሪቱን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም