በክልሉ ምርታማነትን መጨመርና ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ምርታማነትን መጨመርና ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ
ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ምርታማነትና ገቢን ማሳደግ ላይ አመራሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።
የክልሉ የከተማ ልማት ክላስተር በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ፖሊሲ የትኩረት ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ እንደገለጹት፤ በአዲሱ ዓመት አመራሩ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በየዘርፉ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ሥራዎች ላይ በትኩረት ይሰራል።
እንዲሁም የክልሉን የገቢ አቅም ማሳደግ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ገቢ የመሰብሰብ ሥራ ለገቢዎች ተቋም ብቻ የሚተው እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ለዚህም ከላይ እስከታች ያለው አመራር ገቢ የመሰብሰብ ስራውን የራሱ ተግባር አድርጎ መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ማድረግና ገበያውን መግራት እንደሚያስፈልግ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በክልሉ በከተማም ሆነ በገጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በየዘርፉ ቅንጅታዊ ሥራንና ትብብርን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራም አስረድተዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አብዱ ሁሴን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ አሁን እየተወሰደ ያለው የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራትን ለማሻሻል እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በተጨማሪም በኢንዱስትሪ የመልማት እምቅ አቅም ላለው የአማራ ክልል መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በየደረጃው ያለው አመራር በልዩ ክትትል ለተግባራዊነቱ መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አሕመዲን መሐመድ፤ ክልሉን ከችግር ለማውጣት ምርታማነትንና ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት ይገባል ብለዋል።
በከተሞች ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተጀመሩ ሁለንተናዊ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ህገ ወጥነትን በመከላከል በኩል አመራር አባላት ግንባር ቀደም ሆነው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራር አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።