ቅን ኢትዮጵያ ማኅበር   ዜጎችን  ለበጎ ዓላማ እንዲሰለፉ የጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል

 አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ቅን ኢትዮጵያ ማኅበር  ዜጎችን ለበጎ ዓላማ እንዲሰለፉ የጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። 

ቅን ኢትዮጵያ ማኀበር በቅንነት፣ በጎ አሳቢነትና ሠላም ግንባታ ላይ ለተማሪዎች፣ ለወላጅ ተወካዮችና መምህራን ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ዛሬ ተጠናቋል።      

ሥልጠናው ለአንድ ሳምንት የተሰጠ ሲሆን "ተማሪ ለሀገር ሠላም" በሚል መሪ ኃሳብ ተካሂዷል።

የሥልጠናው ተሳታፊዎችም በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሳቢያ፣ የአንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ሥራዎችንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።  


 

የሥልጠናው ማጠቃለያ መርኃ ግብር በአድዋ ድል መታሰቢያ የተካሄደ ሲሆን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።  

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ቅንነት፣ መልካምነትና መተሳሰብ እንደ አገር አብሮ ለመቆም፤ ለዘላቂ ሠላም መረጋገጥ ቁልፍ ሚና አለው።    

ሠላም ደግሞ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ መሰረት ነው ያሉት ከንቲባዋ ሁላችንም ተባብረን መሥራት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።    

ቅን ኢትዮጵያ ማኅበርም የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን በማሰባሰብ ለበጎ ዓላማ እንዲሰለፉ የጀመረው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው ቀጣይነትም ሊኖረው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።   


 

የቅን ኢትዮጵያ ማህበር የቦርድ ሊቀ መንበር መሰረት ስዩም በበኩላቸው የሥልጠናው ተካፋዮች አገር ከእናንተ ብዙ ትጠብቃለች፤ የቀሰማችሁትን እውቀት ወደ መጣችሁበት አከባቢ በማስፋፋት ቅን ማኅበረሰብ የመፍጠር ጥረቱን ማጠናከር አለባችሁ ብለዋል።   


 

የቅን ኢትዮጵያ ማኅበር መሥራች አባል መሰለ ሃይሌ በኢትዮጵያ ቅንነት እንዲዳብር ማህበሩ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።     

ከረጅም ጊዜ አኳያ የቅንነት ባህል እንዲሁም የሠላም እሴቶች መገንባት ላይ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት የግንዛቤ ለውጥ እንዲመጣ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።   

ለአንድ ሳምንት ያህል "ተማሪ ለሀገር ሠላም" በሚል መሪ ኃሳብ የተሰጠው ሥልጠናም የዚሁ አካል ነው ያሉት አቶ መሰለ ይሄው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።  


 

በሥልጠና መርሃ ግብሩ ላይ ወላጆችን ወክለው ከተሳተፉ መካከል ከኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሶኮሩ ወረዳ የመጡት ሙኢዲን አባቦራ አባሱራ፤ ሥልጠናው ለአገሬ በተነሳሽነትና ከልብ በመነጨ ስሜት በትጋት መስራት እንዳለብኝ ግንዛቤ የጨበጥኩበት ነው ብለዋል። 


 

ከአማራ ክልል ባህዳር ከተማ ጊዮን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተወከለችው ተማሪ ትንሳኤ እስጢፋኖስ በበኩሏ በሥልጠና ቆይታዬ አንድነታችንን የበለጠ የሚያጠናክሩ ኃሳቦችን ገብይቻለሁ ብላለች።


 

ከአፋር ክልል ሎጊያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣው ተማሪ ዑስማን መሀመድ በሰጠው አስተያየት በኢትዮጵያን በተሻለ መልኩ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፣ በሠላም በኩልም የሚጠበቅብኝን ድርሻ ላይ በቂ ግንዛቤ ወስጃለሁ ብሏል።

 

 

 

 

  

 

  

 

     

 

 

 

 

 

      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም